ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት ወራት በሁለት ክልሎችና በከተማ አስተዳደሩ 295 ቅሬታዎች እንዲፈቱ አድርጓል- ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ

ድሬዳዋ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ስድስት ወራት በሶማሌና ሀረሪ ክልሎችና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር 295 የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች እንዲፈቱ ማድረጉን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ገለፀ።

የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባኔ ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት በድሬዳዋ፣ በሐረሪ እና በሶማሌ ክልሎች ያከናወናቸውን ዓበይት ተግባራት የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ አለማየሁ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በምሥራቅ የአገሪቷ ክፍል የሚስተዋሉ አስተዳደራዊ በደሎችን ለመከላከል የሚቀርቡለት ቅሬታዎችን መርምሮና አጣርቶ በሚመለከታቸው ተቋማት የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አድርጓል።

በግማሽ በጀት ዓመቱም በአካባቢዎቹ በ95 መዝገቦች የቀረቡለትን የመልካም አስተዳደር አቤቱታዎችን መርምሮ የ295 ሰዎች ጥያቄዎች እንዲፈቱ ማድረጉን ተናግረዋል።

በተሰጠው የመፍትሄ ሐሳብም ከስራ እና ከደሞዝ የታገዱ መምህራን ወደ ስራቸው እንዲመለሱና ውዝፍ ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው ማስደረጉን ለአብነት አንስተዋል።

ከመንግስት ሴክተሮች ባሻገር ተቋሙ አዲስ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ከስምንት የግል ተቋማት የቀረቡለት አቤቱታዎች ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ አስተዳደራዊ በደሎችን ተከላክሏል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ተቋሙ በፌደራል መንግስት ፕሮጀክት ክትትል ስርዓት በተደነገገው አዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት የመንግስት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀትና ጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ክትትል ማድረጉን አስታውቀዋል።

በዚህም በድሬዳዋ ሶስት ግዙፍ የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ ክትትል አድርጎ ፈጣን መፍትሄ እንዲወሰድ አቅጣጫ ማስቀመጡንም አንስተዋል።

በተለይም የሚገነቡ መሠረተ ልማቶች አረጋውያንን፣ አካል ጉዳተኞችንና ህፃናትን ታሳቢ በማድረግና ተጠቃሚነታቸውን ባረጋገጠ መንገድ እንዲተገበሩ ክትትል እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ የተቋሙን የአገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት እና የጀመራቸውን ስራዎች ለማጠናከር በሐረር ንዑስ ቅርንጫፍ ከፍቷል።

በሶማሌ ክልልም ተመሣሣይ ተግባራት ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም