የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ገለጸ።
ባለስልጣኑ ከብሉምበርግ ዓለም አቀፍ የበጎ ፈቃደኞች መርሐ-ግብር ጋር በመተባበር የመንገድ ደህንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ በዚሁ ወቅት፤ እንደገለጹት በከተማዋ የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
ለትራፊክ አደጋ መከሰት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመለየትም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን ጨምሮ የቁጥጥር ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለስልጣኑን ጨምሮ 15 ተቋማትን ያካተተ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት በማቋቋምም የትራፊክ አደጋዎችን መቀነስ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረው በቀጣይም የባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በውይይቱ ጥናት ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት አስተባባሪ ተፈሪ አበጋዝ(ዶ/ር) ከፍጥነት ወሰን በላይ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር የወጡ ፖሊሲዎች ውጤት ማሳየታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የሞት አደጋዎች መቀነስ መቻላቸውን ጠቁመው ቀሪ ስራዎችም በትኩረት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
የብሉምበርግ አለም አቀፍ የበጎ ፈቃደኞች መርሃ-ግብር ዋና ዳይሬክተር ርብቃ ባቪንገር በበኩላቸው የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎች በትኩረት መሰራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የእግረኛ መንገዶች ማስፋትን ጨምሮ ሌሎች የመሰረት ልማቶች የትራፊክ አደጋ እንዲቀንስ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አመርቂ መሆናቸውን ገልጸው የቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡