በሀረና ቡሉቅ ወረዳ ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት በቁ - ኢዜአ አማርኛ
በሀረና ቡሉቅ ወረዳ ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት በቁ
ሮቤ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦በባሌ ዞን ሀረና ቡሉቅ ወረዳ ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ አምስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአገልግሎት በቁ።
"ኢማጅን ዋን ዴይ " በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ትምህርት ቤቶቹ ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡
በምረቃው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የባሌ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሻለ ዲሳሳ በወቅቱ እንደገለጹት፤ መንግሥት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚያደርገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር ወሳኝ ነው።
ለዚህም "ኢማጅን ዋን ዴይ " ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር በዞኑ ሐረና ወረዳ ያስገነባቸው አምስት ትምህርት ቤቶች የዚሁ ጥረት ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
አቶ ተሻለ እንዳሉት፤ ትምህርት ቤቶቹ የተገነቡት ደረጃቸውን የጠበቁ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባልተዳረሰባቸው የዞኑ አርብቶ አደር ማህበረሰብ አካባቢዎች ነው።
መንግስት ባመቻቸው ቦታ የተገነቡት ትምህርት ቤቶች እያንዳንዳቸው ስምንት የመማሪያ ክፍሎች እንዲሁም ቤተ መጽሕፍት፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች፣የመምህራን፣ የአስተዳደር ቢሮዎችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ያካተቱ እንደሆኑ ገልጸዋል
ትምህርት ቤቶቹ ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆናቸው ቀደም ሲል ምቹነት በሌለው ሁኔታ ይማሩ የነበሩ የአካባቢው ተማሪዎች ችግር ማቃለል እንደሚችሉ አመልክተዋል።
የ"ኢማጅን ዋን ዴይ"ድርጅት የኢትዮጵያ ዳሬክተር ሰኢድ አማን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በድርጅቱ ድጋፍ የተገነቡት ትምህርት ቤቶች መንግስት ትምህርትን ለዜጎች ለማዳረስ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማገዝ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በሐረና ቡሉቅ ወረዳ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ጭምር ከ100 ሚሊዮን ብር በሚበልጠ ወጪ አምስት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃታቸው አስታውቀዋል።
ድርጅቱ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ 10 ክልሎች 213 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን አውስተዋል።
በቀጣይም ትምህርት ቤቶች ባልተዳረሰባቸው ገጠራማ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መንግስትን በመደገፍ የማስፋፋት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በባሌ ዞን በየደረጃው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ347 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች በመማር ላይ እንደሚገኙ ከዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።