ሚኒስቴሩ የዘርፉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር አለበት- ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ የዘርፉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር አለበት- ምክር ቤቱ
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመለየትና ችግሮችን በመፍታት ያስመዘገበው ጥሩ ውጤት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ አመት የሥራ ዘመን 16ኛ መደበኛ ስብሰባ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የ2017 የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
በዚሁ ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት በተኪ ምርቶች 2 ቢሊዮን 71 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል።
ዘላቂ ተወዳዳሪነትንና ምርታማነትን የሚያሳድግ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ስራ ላይ መዋሉ በቅንጅት ችግር ይፈጠሩ የነበሩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ማስቻሉን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ127 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በዚህም የተኪ ምርትን መጠንና ገቢን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች በስድስት ወራት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ቶን ምርትን በተኪ ምርት ለመተካት ታቅዶ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን የምርት መጠን መተካት መቻሉን ተናግረዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አማካኝ የማምረት አቅም አጠቃቀም 61 ነጥብ 2 ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው አፈጻጸሙ 98 በመቶ መሆኑን አስታውቀዋል።
በወጪ ንግድ 117 ሺ 586 ቶን ምርት ለመላክ ታቅዶ 95 ሺ 167 ቶን ወይም ከ80 በመቶ በላይ ምርት መላክ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከዘርፉ ለማግኘት ታቅዶ ከነበረው 256 ሚሊዮን 690 ሺ የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 149 ሚሊዮን 334 ሺ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰው አፈጻጻሙ ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፃር ከ6 በመቶ በላይ ከፍ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ የግብዓት አቅርቦትና ትስስርን በተመለከተ በጨርቃጨርቅ ፣ በምግብና መጠጥ ፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንጂነሪንግ ዘርፎች በአጠቃላይ 8 ሚሊዮን 874 ሺ ቶን ግብዓት ለማቅረብ ታስቦ 9 ሚሊዮን 527 ሺ ቶን ቀርቧል ብለዋል።
ለቆዳና ቆዳ ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪዎች 11 ሚሊዮን 700 ሺ ቆዳና ሌጦ ለማቅረብ ታቅዶ 10 ሚሊዮን 400 ሺ ማቅረብ ተችሏል።
መንግስት የወሰዳቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ለዘርፉ አንቀሳቃሾች እስካሁን ያልታየ የገበያ ዕድል ማምጣቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 468 ሚሊዮን 420 ሺ ዶላር ለማቅረብ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአፈጻጸም ረገድ በስድስት ወራት ለዘርፉ አንቀሳቃሾች 369 ሚሊዮን 110 ሺ ዶላር መቅረቡንና የእቅዱን 79 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል።
አፈፃፀሙ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከቀረበው 274 ሚሊዮን 100 ሺ ዶላር ጋር ሲነፃፀር 35 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
የሚኒስቴሩን የዕቅድ አፈፃጸም አስመልክቶ የምክር ቤት አባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አንስተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሁሉም አካባቢዎች ማዳረስ፣ በአገሪቱ የሚመረተው የቆዳ ምርት ለምን በሚፈለገው ልክ አልተሰራበትም፣ የዘርፉን የፋይናንስ ማነቆ ለመፍታት እና በታዳሽ ሃይል ላይ ምን ተሰራ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያና ምላሽ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከሥራ ውጪ የነበሩ በርካታ ተቋማት ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትና ምርታማነት እንዲረጋገጥ መንግስት የዘርፉን ችግሮች በመፍታት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በቆዳ ምርት ላይ ያለውን ችግር በመለየት መዋቅራዊ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ታዳሽ ሃይልን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በምክር ቤቱ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አማረች በካሎ (ዶ/ር) ሚኒስቴሩ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመለየትና በመፍታት ያስመዘገበው ጥሩ አፈጻጸም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ሚኒስቴሩ የተጣለበትን ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣቱንና እና ጠንካራ የሆነ ቅንጅታዊ አሰራርን መከተሉን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪዎችን አቅም በማሳደግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትስስራቸውንና አፈጻጸማቸውን የበለጠ ማጠናከር ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።