የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርን ለማሳካት በዘርፉ የተካነ ዜጋን ለማፍራት ጥረት እየተደረገ ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርን ለማሳካት በዘርፉ የተካነ ዜጋን ለማፍራት ጥረት እየተደረገ ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር ዕውን ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተካነ ዜጋ ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ የተደረገው የ''አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ’’ መርኃ ግብር በኢትዮጵያ መንግስትና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ትብብር የተጀመረ የዲጂታል ሥራ ክህሎት ማሳደጊያ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ "ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በዚህም ዛሬ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የኮደርስ ስልጠና የወሰዱ 180 ሙያተኞቹን አስመርቋል።
የኢኖቬንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር በቴክኖሎጂን የተካነ ዜጋን ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጓል።
አምስት ሚሊዮን ኮደርሶችን የዚህ አካል መሆኑን ገልጸው፤ ካሳለፍነው ከሐምሌ ወር ጀምሮ 470 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ሰልጣኞቹ መጪውን የዲጂታል ዘመን ታሳቢ በማድረግ ክህሎታቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ዕድል እንዳገኙ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ የተማረ ወጣት ኃይል ያላት ሀገር በመሆኗ በአለም ላይ የሚፈጠረውን የስራ ዕድል ለመቀላቀልም ስልጠናው ሰፊ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳዳሩ ስማርት ሲቲን ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት እንደ ተቋም ተመራቂዎቹ ፈር ቀዳጅ ናቸው ብለዋል።
ኤጄንሲው ሰራተኞች የኮደርስ ስልጠና መውሰዳቸው በከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ውስጥ የአገልግሎት አሰጣጥን ከማሻሻል ረገድ በርካታ ውጤቶችን እንደሚያመጣ ተናግረዋል።
በሒደትም ሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች ዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትና ክሕሎት አዳብረው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግም ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አማረ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎቹ ከ180 የተቋሙ ሰራተኞች በአራት የስልጠና ዘርፎች ስልጠናውን የተከታተሉ ናቸው ብለዋል።
በመዲናዋ እስከ በጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ድረስ 75 ሺህ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ስልጠናው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በዚህ መሰረትም በኤጀንሲው የሚሰጡ አገልግሎቶች በተሻለ አቅም እንዲሰጡ ከማድረግ አንፃር ስልጠናው ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ነው የገለጹት።