ምርት ገበያው የግብይት ስርዓቱን ወደ ቀጥታ በይነ መረብ ማሸጋገሩ ተወዳዳሪነቱን ያሳድጋል- ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ምርት ገበያው የግብይት ስርዓቱን ወደ ቀጥታ በይነ መረብ ማሸጋገሩ ተወዳዳሪነቱን ያሳድጋል- ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ስርዓቱን ከኤሌክትሮኒክ ወደ ቀጥታ በይነ መረብ ማሸጋገሩ የምርት ገበያውን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚያስገነባውን የባለ 24 ወለል ሁለገብ ሕንፃ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባለ24 ወለል ሁለገብ ሕንጻው በሶስት ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቃ ነው።
ሕንጻው ቢሮዎች፣ የስብሰባ አዳራሽና ጅምናዚየም ያሉትና አካል ጉዳተኞችን ያማከለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ነው ብለዋል።
ምርት ገበያው ከኤሌክትሮኒክ የግብይት ሥርዓት ወደ ቀጥታ በይነ መረብ(ኦንላይን) ግብይት ሥርዓት ማሸጋገሩንም ጠቅሰው፤ ይህም ተገበያዮች ባሉበት ቦታ ሆነው ግብይት መፈጸም ያስችላቸዋል ብለዋል።
መንግስት የውጭ ባለሃብቶች በጅምላ ንግድ እንዲሳተፉ መፍቀዱን አስታውሰው፤ የተጀመረው የቀጥታ የንግድ ግብይት ምርት ገበያውን ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት እንደሚሳድግ ተናግረዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕውን ለማድረግም በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።