ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳለጥ አምራች ኢንዱስትሪውን ማቀናጀት ላይ ትኩረት ተሰጥቷል  

አርባ ምንጭ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳለጥ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማቀናጀት ላይ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪው የወጪ ምርት ከ700 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር መገኘቱም ተመላክቷል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ በአርባ ምንጭ ከተማ የተቋሙን የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

በዚሁ ወቅት የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቦጋለ ቦሼ እንደገለጹት አምራች ኢንዱስትሪውን በማቀናጀት በኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ እየተሰራ ነው።

ለዚህም የክልሉን እምቅ ሀብት በኢንዱስትሪ ልማት እሴት ጨምሮ በማምረት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ማጉላት ይጠይቃል ብለዋል።

በአርባ ምንጭ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በዲላ፣ በጂንካና በሌሎች ከተሞች መለስተኛ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት የሀብት ምንጭ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት የተገኘባቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የክልሉ መንግስት የመሬት አቅርቦት እና የገበያ ትስስር በመፍጠር የቴክኖሎጂ ሽግግር እውን ለማድረግ መስራቱንም ጠቅሰዋል።

ኢንዱስትሪ የኢኮኒሚ እንቅስቃሴን ለማፋጠን ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ እንደ ሀገር የተጀመረውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለማሳካት እየሠራን ነው ብለዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ክልሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ያለውን አቅም በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን ለማበረታታት መስራቱንም አንስተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪው የወጪ ምርት ከ700 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን ገልጸዋል።

በአልሚ ባለሀብቶች ከ23 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት ወደ ጣሊያን፤ የሞሪንጋ እና ሸማ ሥራዎችን ደግሞ  ለአሜሪካና አውሮፓ ገበያዎች በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ጠቁመዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ የአምራች ኢንዱስትሪ ሼዶችን ለማጠናቀቅ 60 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉንም ተናግረዋል።

በአርባ ምንጭ፣ ዲላና ጂንካ ከተሞች አልሚ ባለሀብቶችና ኢንተርፕራይዞች ሥራ መጀመራቸውን ጠቁመው፣ ለ800 ሴት አርሶ አደሮች የሥራ ዕድል የፈጠረው የዘይሴ ወዘቃ ሞሪንጋ ማቀነባበሪያ ፕሮጀክትን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ክልሉ በግማሽ በጀት ዓመቱ ለ128 ኢንተርፕራይዞች 43 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር መፍጠሩንም አቶ ጥላሁን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም