ቀጥታ፡

የፐብሊክ ሰርቪስና ትራንስፖርት አገልግሎት ተደራሽነቱን በማስፋት አስተማማኝና ፈጣን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፡- የፐብሊክ ሰርቪስና ትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽነት በማስፋት ምቹ አስተማማኝና ፈጣን ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን የትራስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።

ፐብሊክ ሰርቪስና ትራንስፖርት አገልግሎት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተወያየ ይገኛል።

በመርሃ ግብሩ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር)፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ጅግሶ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረኦ ሀሰን በመድረኩ እንደተናገሩት፤ የትራንስፖርት ዘርፉ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።


 

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎቱን ምቹ፣ አስተማማኝና ፈጣን እንዲሆን እንዲሁም ዜጎች ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በሚቆጥብ መልኩ የትራንስፖርት ተሽከርካሪ ቁጥርን በመጨመርና አገልግሎቱን ተደራሽ እየተደረገ ነው።

የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃውንም በትራንስፖርት አገልግሎት አይነት፣ በምልልስ መጠን በመንገድ አቅርቦትና ሽፋን ተደራሽነቱ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን አክለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማና ፌዴራል ተቋማት የመንግስት ሰራተኛው ትራንስፖርት ጫናን ለመፍታት የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 489/2014 እንደገና እንዲቋቋም መደረጉን አስታውሰዋል።

የምክክር መድረኩ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጠው አገልግሎት ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር ያለመ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም