ባለፉት ስድስት ወራት 217 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቧል - የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት 217 ሺህ ዩኒት ደም ተሰብስቧል - የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት
አዲስ አበባ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፡- በበጀት ዓመቱ ያለፉት ስድስት ወራት 217 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።
የደም ልገሳ አገልግሎት በወሊድ ምክንያት ደም ለሚያስፈልጋችው እናቶች፣ ህጻናትና እንዲሁም ድንገተኛ አደጋ ለደረሰባቸው ዜጎች በመድረስ ህይወትን የመታደግ በጎ ተግባር ነው።
የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት የህብረተሰቡ ደም ልገሳ ባህል በግንዛቤ ፈጠራ ስራ የማዳበር፣ በጎ ፊቃደኛ ደም ለጋሾች ቁጥር እንዲጨምር ማስቻል፣ ደም ለጋሾችን በመመርመርና ጥራቱን የጠበቀ ደም በመሰብሰብ ለተጠቃሚዎች እና ጤና ተቋማት የማዳረስ ስራ ይሰራል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው(ዶ/ር) በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ዕቅድ ክንውን ዙሪያ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ግማሽ ዓመት 240 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ 217 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
የግማሽ ዓመቱ ዕቅድ ክንውን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ48 ሺህ ዩኒት ደም ብልጫ መኖሩን ገልጸው፤ ጥቅል አፈጻጸሙን 90 በመቶ ማድረስ እንደተቻለም አመላክተዋል።
ይህም የደም ለጋሽ በጎ ፊቃደኞችን ቁጥር ለመጨመር በተሰራው የግንዛቤ ፈጠራ ስራና የደም ባንክ አገልግሎት ተደራሽነቱን በማስፋት የተገኘ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም በሀገሪቱ 48 ደም ባንክ ቅርንጫፎች የነበሩ ሲሆን በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ዕቅድ ክንውን በኦሮሚያና አፋር ክልሎች አምስት ደም ባንክ ቅርንጫፎችን በመጨመር ቁጥሩን ወደ 53 ከፍ እንዲል መደረጉን አስታውቀዋል።
በሁለተኛው ግማሽ ዓመት ዕቅድም ተጨማሪ ደም ባንኮች በክልሎች የማስፋፋት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የተቋሙ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ዕቅድ ክንውን ከተቋሙ ዕቅድ አኳያ የተሳካ ቢሆንም ግን በሀገሪቱ ከሚፈለገው ደም አንጻር ገና ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ አክለዋል።
በሀገሪቱ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ያሉ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሽ ተማሪዎችና ወጣቶች በሚለግሱት ደም የበርካታ ዜጎች ህይወት በመታደግ ላይ እንደሚገኙ አክለዋል።
ወጣቶችና ተማሪዎች እያደረጉ ያለውን በጎ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበው፤ ማንኛውም ጤነኛ ሰው በዚህ በጎ ተግባር ላይ በመሳተፍ ውድ የሆነውን የሰው ሕይወት ለማዳን ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።