በሐረር ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ - ፖሊስ

ሐረር፤ጥር15/2017 (ኢዜአ)፦በሐረር ከተማ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ጣሰው ቻለው እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ዛሬ ሌሊት 8፡00 ሰዓት ላይ በከተማው ስላሴ ቤተክርስትያን አደባባይ ላይ ነው።

የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-06621 ድሬ የሆነ እና በሬ የጫነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪን ለማዳን ሲሞክር በመገልበጡ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል።

በአደጋውም በአይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ የነበሩ ሁለት ሰዎች ህይወት ወድያው ሲያልፍ በአንድ ሰው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

በአይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ ከተጫኑት 15 በሬዎች መካከልም ሶስቱ መሞታቸውንም ገልጸዋል።

የአይሱዙ አሽከርካሪው ለጊዜው መሰወሩን ጠቁመው፤ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪው በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት መሆኑን ኮማንደር ጣሰው ተናግረዋል።





 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም