የፕሪሚየር ሊጉ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ፤ ጥር 15/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ16ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
የ16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በአርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ መካከል ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋል።
አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው ያለፉት ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ወላይታ ድቻ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ቡድኑ በአምስቱ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን አስቆጥሮ አምስት ጎሎች ተቆጥረውበት በ20 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ16ኛ ሳምንት ሁለተኛ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ስሑል ሽሬ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ድል ያስመዘገበው በአንዱ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በአምስቱ ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሶስት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ14 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ስሑል ሽሬ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል።
በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ11 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
የ16ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥር 18 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል። ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ የሳምንቱ አራፊ ቡድኖች ናቸው።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ መድን፣ መቻል እና ሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 26 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
የድሬዳዋ ከተማው መሐመድ ኑር ናስር፣ የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፍጹም ጥላሁን እና የመቻሉ ሽመልስ በቀለ በተመሳሳይ ስድስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በጋራ እየመሩ ነው።