የተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን እንድትቀላቀል ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን እንድትቀላቀል ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦ ሩሲያ፣ ጃፓን እና ዩናይትድ ኪንግደም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል የጀመረችውን ሂደት እንዲደግፉ አስታውቀዋል።
የንግድ ድርጅቱን በመቀላቀል ሂደት ውስጥ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በጄኔቫና ኦስትሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው ተቀማጭነታቸውን በጄኔቫ ካደረጉ የተለያዩ ሀገራት ቋሚ መልዕክተኞች ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ፀጋአብ ውይይቱን ያደረጉት ከሩሲያ አምባሳደር ኒኮላይ ፕላቶኖቭ፣ ከጃፓን አምባሳደር ናኦኪ ሂኮታ እና ከዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር አንድሪው ጃክሰን ጋር ነው።
አምባሳደሩ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን የመቀላቀል ሂደት ውስጥ ወሳኝ ወደ ሚባለው ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።
ድርጅቱን የመቀላቀል እቅዱ እውን እንዲሆን ቁልፍ ከሆኑ የንግድ አጋር አገራት ጋር የሚደረጉ የሁለትዮሽ ድርድሮች ወሳኝ እንደሆኑ አመልክተዋል።
የሩሲያ፣ ጃፓን እና ዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደሮች ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት እንድትቀላቀል እና አባል የመሆን ሂደቱን እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
ሀገራቱ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩ እና ኢትዮጵያ የአባልነት ፍላጎቷ እንዲሳካ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ከጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።