ቀጥታ፡

ደም ባንኮች ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡት ደም የጥራት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፡- ደም ባንኮች ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡት ደም ትክክለኛና የጥራት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለክልል ደም ባንኮች የህክምና መሳሪያዎችንና የግብዓት ድጋፎችን አድርጓል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው(ዶ/ር)፣ የክልል ጤና ቢሮዎች እና ደም ባንክ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡


 

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ የደም ባንክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ የሚገኙ ደም ባንኮች ወቅቱንና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ግብ በማስቀመጥ የደም መለገሻ ግብዓቶችን በ128 ሚሊዮን ብር መግዛታቸውንም ገልጸዋል፡፡


 

ግብዓቶቹ የለጋሾችን ደም ለመመርመሪያነት የሚያገለግሉ ግብዓቶች፣ ማስቀመጫ ፍሪጆችንና ማጓጓዣን ጨምሮ ሌሎች ለአገልግሎቱ መስጫነት የሚውሉ መሆኑም ተጠቅሷል።

ደም ባንኮች ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡት ደም ትክክለኛና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የሚደርጉ ድጋፎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው(ዶ/ር) በበኩሉ የቀረቡት ቁሳቁሶች በበጀት ዓመቱ ለማቅረብ በእቅድ የተያዘውን ያሳኩ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡

የህክምና ቁሳቁሶቹ ጥራታቸውን የጠበቁና በሀገሪቱ ጥራቱን የጠበቀ ደም ባንክ አገልግሎት እንዲኖር የሚያስችሉ መሆናቸውንም ተናግርዋል።

ተቋማቱ ግብዓቶቹን በአግባቡ ተጠቅመው ለታለመላቸው ዓላማ ማዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት እና ጤና ሚኒስቴር በጋራ የገዟቸውን ግብዓቶች ሁሉም ክልሎችና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በዛሬው ዕለት ተረክበዋል፡፡

በደም እጦት የሚሰቃዩ በአብዛኛው በወሊድ ወቅት ደም የሚፈሳቸውን እናቶችንና ህጻናትን ህይወት ለመታደግ የህብረተሰቡ የደም ልገሳ ባህል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም መልዕክት ተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም