ቀጥታ፡

የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማሩ ቁልፍ ማሻሻያዎች ተደርገዋል - ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማሩ ቁልፍ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮ ጃፓን የንግድና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት ባለሀብቶች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ ገለጻዎች ተደርገዋል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፈጣን እድገት ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማሩ ቁልፍ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም አንስተዋል።

የሀገሪቱን እድገት ለማጎልበት ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያሉ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያና ጃፓን በመተማመን፣በመከባበር እና የጋራ የልማት ራእይ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶም ጃፓን በቴክኖሎጂና በልማት ትብብር ለሚደረገው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑንም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ የጃፓን ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራታቸውን ገልጸው፥ አሁንም ተጨማሪ ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅቱ አገራት ተቀራርበው የሚሰሩበት እና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሆነበት መሆኑን ገልጸው፥ ለዚህም ኢትዮጵያ በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሯን አመላክተዋል።

በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ፥ኤምባሲው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለጃፓን ባለሀብቶች በማስተዋወቅ ረገድ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ወሳኝ የሆነውን ይህንን የንግድና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየም ለማካሄድ ከጃፓን እና ከኢትዮጵያ ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጋር በትጋት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ለሲምፖዚየሙ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ሲምፖዚየሙ በአስፈላጊ ወቅት መካሄዱን የጠቀሱት ደግሞ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ናቸው።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለስራ እድል ፈጠራ እና የሀገሪቱን የውጭ ንግድ ለማሳደግ ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን እንድታሳካ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለንግድ ስራ ምቹ እና ወደ ብሩህ አቅጣጫ እየገሰገሰች መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም