አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን የአመራሩ ድርሻ የጎላ ነው - ኢንስቲትዩቱ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን የአመራሩ ድርሻ የጎላ ነው - ኢንስቲትዩቱ
አሶሳ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን የአመራሩ ድርሻ የጎላ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ አዲሱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የትውውቅ መድረክ በአሶሳ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) እንዳሉት አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መዘጋጀቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገትን ለማረጋገጥ ያግዛል።
ፖሊሲው ለሀገራዊ ሥርዓተ ምግብ መሻሻል እንዲሁም የምግብ ዋስትናና የምግብ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸው፤ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ዘላቂ አጠቃቀም እንደሚያሳድግም ተናግረዋል።
ፖሊሲው ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።
ፖሊሲው አርሶ አደሩ መሬቱን ተጠቅሞ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝና የገጠሩን ህዝብ የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻል መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እነዚህን ሁሉ ጥቅሞች የሚያስገኘው አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን የአመራሩ ድርሻ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢንስቲትዩቱ የፖሊሲ ጥናት እና የምግብ ስርዓት ዳይሬክተር አቶ ረታ ዋጋሪ በበኩላቸው አመራሩ የፖሊሲውን አስፈላጊነት እስከታችኛው መዋቅር ማሳወቅ ይጠበቅበታል ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለግብርና ስራ ምቹ መሆን ጠቁመው፤ ፖሊሲው በክልሉ የግብርና ዘርፉን በማዘመንና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በማጠናከር አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እንደገለጹት፤ አዲሱ የግብርና ልማት ፖሊሲ ዘርፉ የሚመራበትን መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የጎላ ድርሻ አለው።
ፖሊሲው መዘጋጀቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ መዋቅራዊ ማነቆዎችን እንደሚፈታ ተናግረው፤ ዘርፉ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ የሚያስች ነው ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሃሊፋ በበኩላቸው ፖሊሲው በክልሉ ያለውን የግብርና አሰራር የሚያሻሽል እና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።
ፖሊሲው ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ እና የግሉ ዘርፍ በግብርናው መስክ በስፋት እንዲሰማራ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።
የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማጎልበት በክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያደገ የመጣው ምርትና ምርታማነት የበለጠ እንዲጨምር እንደሚያግዝ በመጠቆም።
ቢሮው ለፖሊሲው ተግባራዊነት ከግብርና ባለሙያዎች እና አርሶ አደሩ ጋር በቅርበት እንደሚሰራም አቶ ባበክር ጠቁመዋል።