ቀጥታ፡

ለአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ለሚመጡ እንግዶች ፈጣን የመዳረሻ ቪዛ ለመስጠት በቂ ዝግጅት ተደርጓል

 

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ህብረት ጉባዔን ለመታደም ወደ አዲስ አበባ ለሚመጡ እንግዶች ፈጣንና ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገለጹ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በመጪው የካቲት ወር በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች ፈጣንና ቀልጣፋ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለእንግዶች አገልግሎቱን የሚሰጡ 124 ባለሙያዎች የዲፕሎማቲክ ፕሮቶኮል፣ የቱሪዝምና ማርኬቲንግን ጨምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ይህም ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች ብቁና ተወዳዳሪ አገልግሎት ለመስጠትና የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር ያግዛል ብለዋል።

ከሰው ሃይል ስልጠናው ባለፈ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንና በአግባቡ መምራት የሚቻልበት ሁኔታ መዘርጋቱንም አንስተዋል።

ከተለያዩ አገራት ህጋዊ ፓስፖርት ይዘው ለሚመጡ እንግዶች የመዳረሻ ቪዛ (Visa on Arrival) ለመስጠት የሰው ሃይልና የቴክኖሎጂ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ በተያዘው ጥር ወር የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት ለመጀመር አቅዶ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲሰራ እንደነበር ዋና ዳይሬከተሯ አስታውሰዋል።

በዚህ መሰረት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የኢ-ፓስፖርት ቡክሌቶች ተመርተው ከውጭ መግባታቸውንና የቴክኖሎጂና የሰው ሃይል ስልጠና መጠናቀቁንም አመልክተዋል።

ከመጪው የካቲት ወር ጀምሮ ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች ለ10 ዓመታት የሚያገለግለው ኢ-ፓስፖርት አገልግሎት እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም