ቀጥታ፡

የከተማዋን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን ለአደጋ ምላሽ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው- ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከተማዋ የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ለአደጋ ምላሽ ዘርፍ አገልግሎት የሚውሉ የማሽነሪና ቁሳቁስ ድጋፎችን ከፖላንድ መንግሥት ተረክቧል።


 

ድጋፉ PCPM ከሚባል የፖላንድ መንግስት አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት እና IIRR ኢንተርናሽናል ኢንስቲትዩት ኦፍ ሩራል ሪኮንስትራክሽን ለኮሚሽኑ አመራሮች አስረክበዋል።

ቁሳቁሶቹ በአደጋ ወቅት የሚደረጉ የግል መከላከያዎች እና የእሳት ማጥፊያ መሳሪያዎች፣ የህክምና አቅርቦቶችና መሰል ለአደጋ ምላሽ ዘርፍ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው።

የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍቅሬ ግዛው በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ኮሚሽኑ አዲስ አበባ የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት ከአጋር አካላት ጋር እየሰራ ነው።

በዚህም በሰው ህይወት፣ ንብረትና የልማት አውታሮችን ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በፖላንድ መንግስት የተደረገው ድጋፍ ተቋሙ በአደጋ ምላሽ ለሚያከናውነው ስራ አቅም እንደሚጨምርለት አስታውቀዋል።


 

የIIRR የፕሮግራም ዳይሬክተር ወርቅነህ ንጋቴ(ዶ/ር) የፖላንድ መንግስት ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለተቋሙ የተደረገው ድጋፍ በአደጋ ወቅት የተሟላ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ ጠቅሰው በቀጣይ ከተቋሙ ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም