ቀጥታ፡

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ከጅቡቲ ወደቦችና ነፃ ዞኖች ባለስልጣን ሊቀመንበር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ከጅቡቲ ወደቦች እና ነፃ ዞኖች ባለስልጣን ሊቀመንበር አቡበከር ኦማር ሃዲ ጋር በወደብ አገልግሎት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ብርሃኑ በውይይቱ የዶራሌህ ሁለገብ ወደብ እ.አ.አ በ2024 የስራ ዘመን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የካርጎ ኮንቴይነሮችን በማስተናገድ ለሰጠው ውጤታማ አገልግሎት ምስጋና አቅርበዋል።

በ2025 የፈረንጆቹ ዓመት ከጂቡቲ ወደቦች ወደ ኢትዮጵያ ለሚኖረው ከፍተኛ የአፈር ማዳበሪያ ጭነት ዝውውር የወደቡ የአገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።


 

በተጨማሪም የጅቡቲ-ዲኪል-ጋላፊ ዋና መንገድ ግንባታ ያለበት ደረጃ፣ የጣናነሽ ጀልባ ወደ አገር ቤት የማጓጓዝ ሂደት እንዲሁም ለረጅም ጊዜ የቆዩ ጭነቶችን ወደ ኢትዮጵያ በፍጥነት ማጓጓዝ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም