ቀጥታ፡

በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ አቋም መያዝ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራራቢ አቋም መያዝ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ወሳኝ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ገለጹ።

በተለያዩ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው ሁለተኛው የፓርላማ የዜጎች ፎረም እየተካሄደ ነው፡፡


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) 'ብሔራዊ መግባባት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና' በሚል ርዕስ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብዙሃኑ ህዝብ ተቀራራቢና ተመሳሳይ አቋም መያዝ አለበት ብለዋል።

እንደ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመቀጠል የጋራ ማንነትና ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚገባም የተለያዩ ሀገራትን ተሞክሮ ጠቅሰው አብራርተዋል።

የህዝብ ማንነት፣ መንግስታዊ መዋቅር፣ የሀገር የግዛት አንድነት ላይ ዜጎች የጋራ መግባባት ሊይዙ ይገባል ብለዋል።

በፎረሙ 'የብሔራዊ መግባባት ታሪካዊ መሰረቶች' በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ያቀረቡት በሚኒስትር ማዕረግ የብልፅግና ፓርቲ ጥናትና ምርምር ኃላፊ አብዲዋሳ አብዱላሂ (ዶ/ር) ናቸው።

እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት መሆኗ የውጭ ወረራዎችን መቋቋምና በአለምአቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መስራች አባልነቷ የብሔራዊ መግባባት ማሳያዎች ናቸው።

ሀገሪቱ ያላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችም ለብሔራዊ መግባባት መሰረቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የነበሩ ጥንካሬዎችን የበለጠ ማስቀጠልና ያልተዳሰሱትን ማካተት የጋራ መግባባት ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) 'የሀገራዊ መግባባት ፈተናዎች' በሚል የተለያዩ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው የውይይት መነሻ አቅርበዋል።

ሀገረ መንግስቱን የሚፈትኑ ጉዳዮች ላይ የማይታረቅ አቋም መያዝ፣ ርዕዮተ አለምን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ፅንፈኝነት፣ መጠራጠርና የመንግስት ቅቡልነት ማጣት እንዲሁም የሀሰተኛ መረጃ መበራከት የብዙ ሀገራት የብሔራዊ መግባባት ፈተና ናቸው ብለዋል።

የዓለም አቀፍ ሁኔታና የተገዳዳሪ ሃይሎች ፍላጎት፣ የትምህርት ደረጃና የህብረተሰቡ ንቃተ ህሊና እንዲሁም የደህንነትና የፀጥታ ስጋት የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት ላይ ስጋት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህን ዓለም አቀፍ ሁኔታ በመገንዘብ ለጋራ መግባባት መስራት ይገባል ብለዋል።

የመጀመሪያው የዜጎች የፓርላማ ፎረም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ አተኩሮ ከአንድ ወር በፊት መካሄዱ ይታወሳል።

የፓርላማ ዜጎች ፎረም በቀጣይ በየወሩ ለሀገርና ለአህጉሪቷ በሚበጁ ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ውይይት የሚካሄድበት ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም