የኢትዮ-ጃፓን የንግድና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ጃፓን የንግድና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ጃፓን የንግድና ኢንቨስትመንት ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አርጋ፣ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት ባለሀብቶች እየተሳተፉ ናቸው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢኮኖሚው መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።
በማሻሻያውም የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እንዲሰማሩ ቁልፍ ማሻሻያዎች መደረጋቸውንም አንስተዋል።
ሲምፖዚየሙ ኢትዮጵያ እና ጃፓን የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማጠናከር ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው ሲምፖዚየሙ የጃፓን ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት እና የንግድ እድሎች ለመዳሰስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ጃፓን በመተማመን፣ በመከባበር እና የጋራ የልማት ራእይ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸው ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶም ጃፓን በቴክኖሎጂና በልማት ትብብር ለሚደረገው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ የጃፓን ኢንቨስትመንቶች መኖራቸውን ገልጸው አሁንም ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ወቅቱ አገራት ተቀራርበው የሚሰሩበት እና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሆነበት መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ኢትዮጵያ በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሯን አመላክተዋል።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጃፓን ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ፍሬያማ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በጃፓን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት እድሎችን ለጃፓን ባለሀብቶች በማስተዋወቅ ረገድ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬው መድረክም የዚሁ አካል መሆኑን አንስተዋል።
ሲምፖዚየሙ በአስፈላጊ ወቅት መካሄዱን የጠቀሱት ደግሞ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ናቸው።
የጃፓን የግል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን መሻሻል እና ለውጥ መገንዘብ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያ የተሰማሩ የጃፓን ኩባንያዎች ትልቅ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትልቅ ለውጥ መሆኑንም ገልጸዋል።