ቀጥታ፡

የእስያ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደሚሻ ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦የእስያ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር በኢንቨስትመንት መስክ በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ ልዑክ ከእስያ የመሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዝዳንት ጂን ሊኩን እና ከሌሎች የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በቤጂንግ ተወያይቷል።

ውይይቱ ባንኩን ጨምሮ ባለሀብቶች፤ በተለያዩ አገራት የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችና ተቋማት በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት እድል መጠቀም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ለባንኩ ከፍተኛ አመራሮች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

 


 

የእስያ የመሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት ባንክ የኢንቨስትመንት ኦፕሬሽን ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዝዳንት ራጃት ሚስራ በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችንም አድንቀዋል።

የባንኩ ፕሬዝዳንትና አመራሮች የኢንቨስትመንት አማራጮችን በጥልቀት በመመልከት ከኢትዮጵያ ጋር ትብብር ለመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራ ልዑክ በቻይና የስራ ጉብኝት እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የእስያ የመሰረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት ባንክ ጂን ሊኩን በህዳር ወር 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ ከገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና ከተለያዩ የመንግስት አመራሮች መወያየታቸው የሚታወስ ነው።

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ እ.አ.አ በ2016 የተቋቋመ ሲሆን ዋና ቢሮውን በቻይና ቤጂንግ አድርጓል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ 110 አገራት የዓለማችን ሁለተኛው ግዙፍ የባለብዝሃ ወገን ልማት ባንክ አባል ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም