የአልጄሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች እንደሰማሩ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የአልጄሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች እንደሰማሩ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017 (ኢዜአ):- የአልጄሪያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ዕድሎች ተጠቅመው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሙሃመድ ጠየቁ።
አራተኛው ዓለም አቀፍ የግንባታ፣ ኮንስትራክሽን እና የከተማ ልማት ኤግዚቢሽን በአልጄሪያ ምስራቃዊ ክፍል በምትገኘው የአነባ ግዛት ዋና መቀመጫ አነባ ከተማ ተካሄዷል።
በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሙሃመድ በኤግዚቢሽኑ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና አልጀሪያ በዲፕሎማሲ ረገድ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን አውስተዋል።
የአልጄሪያ ባለሀብቶች በአዲስ አበባ በቀጣይ በሚካሄደው የሁለቱን አገራት የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጋብዘዋል።
ጉብኝቱ ለድርጅቶቹና ለባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎች ለማየት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው አመልክተዋል።
አምባሳደር ሙክታር ከኤግዚቢሽኑ ጎን ለጎን በተለያዩ በኮንስትራክሽን ግብዓቶች እና ቁሳቁሶች ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከተሰማሩ የአልጄሪያ ድርጅቶች እና ባለሀብቶች ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደሩ በውይይቱ ስለ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድሎች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ሚሲዮኑ ለባለሀብቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በኤግዚቢሽኑ ላይ በርካታ ኩባንያዎች ከመደበኛ እስከ ስማርት መኖሪያ ቤቶች እና ሪል ስቴቶች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች እና ግብዓቶች ለእይታ ማቅረባቸውን በአልጀርስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።