ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቀነስ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር አለባቸው - ኢጋድ

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፡-የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቀነስ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በቅንጅት የሚሰሯቸውን ስራዎች ማጠናከር እንዳለባቸው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 69ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም ዛሬ ተጠናቋል፡፡

በፎረሙ በቀጣዮቹ ወራት የሚኖረው ቀጣናዊ የአየር ትንበያ ይፋ ተደርጓል ።


 

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ምክትል ዋና ጸሐፊ ሙሀመድ አብዲ ዋሬ በወቅቱ እንደገለጹት የአየር ንብረት ለውጥ በቀጠናው ሀገራት ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን እያደረሰ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የቀጣናው ሀገራት በተናጥል ሳይሆን በጋራና በተቀናጀ መልኩ ተጽኖውን መቀነስ ላይ መስራት እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡ 

የቀጣናው ሀገራት የሚቲዎሮሎጂ ተቋማት የሚተነብዩትን ትንበያ በመውሰድ መጠቀም እንደሚገባ የገለጹት ምክትል ጸሀፊው በተለይ መረጃዎችን ለተጠቃሚው በማድረስ በኩል በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት እያከናወነችው ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን አንስተው ተግባሩን አጠናክራ መቀጠል እንደሚገባትም አመላክተዋል፡፡

ኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል ተወካይ ሃላፊ አብዲ ፊዳር (ዶ/ር) በበኩላቸው አለምን እየፈተነ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ፈጣና ትኩረት እንደሚያስፈልገው አመላክተዋል።

ኢጋድ ከመጋቢት አስከ ግንቦት የተነበየውን የአየር ጠባይ ትንበያ የአባል አገራት በመውሰድ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በወቅቱና በአግባቡ ማድረስ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በዚህም የግብርና እንቅስቃሴውን በአየር ንብረት ትንበያ ላይ ተመስርቶ  እንዲያከናወን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት ከሚያሳድርባቸው የቀጣናው ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ የአየር ትንበያን ማዘመንና የመረጃ ተደራሽነትን ማስፋት ላይ መሰረት አድርጋ እየሰራች እንደምትገኝ አስታውቀዋል ።

ራዳርን ጨምሮ ዘመናዊ የአየር ምልከታ መከታተያ መሳሪያዎችና ማዕከላት እየተተከሉ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

በፎረሙ የዘርፉ ተመራማሪዎች ፖሊሲ አውጪዎችና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም