ፋሲል ከነማ እና መቻል አቻ ተለያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ፋሲል ከነማ እና መቻል አቻ ተለያዩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ፋሲል ከነማ እና መቻል ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ በረከት ደስታ በ38ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል መቻልን መሪ አድርጋ ነበር።
ይሁንና ከእረፍት መልስ አንዋር ሙራድ በ70ኛው ደቂቃ ከመረብ ላይ ያሳረፋት ጎል ለፋሲል ከነማ አንድ ነጥብ አስገኝታለች።
ውጤቱን ተከትሎ መቻል በ26 ነጥብ ተመሳሳይ ነጥብ ባለው የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
መቻል ዳግም የሊጉን መሪነት መረከብ የሚችልበትን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ፋሲል ከነማ በ17 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቀን ላይ በተደረገ ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
የዛሬ ጨዋታዎችን ተከትሎ የ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል።
የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ከጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳሉ።