ቀጥታ፡

ገቢ የመሰብሰብ አቅምን የሚያሳድጉ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላሉ - የብሄራዊ ታክስ ሪፎርም ግብረ ኃይል

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፡- ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ልማትን ጨምሮ የገቢ አሰባሰብ አቅምን የማጎልበት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥሉ የብሄራዊ ታክስ ሪፎርም ግብረ ኃይል አስታወቀ።

አዳዲስ ታክስ ከፋዮች ወደ ታክስ ስርዓቱ እንዲገቡ ክትትል እንደሚደረግም ገልጿል።

የብሄራዊ ታክስ ሪፎርም ግብረ ኃይል የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ በጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ዛሬ አካሂዷል፡፡

ግብረ ኃይሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከጉምሩክ ኮሚሽን በተወጣጡ ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚመራ ነው።

በግምገማውም የበጀት ዓመቱ የገቢ አሰባሰብ በእቅዱ መሰረት በተሳካ ሁኔታ መፈጸሙን ግብረ ኃይሉ ገልጿል።

በቀሪ የበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በእቅድ የተያዘውን የገቢ እቅድ ለማሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጧል።

ለገቢ አሰባሰቡ አጋዥ የሆኑ የስጋት ስራ አመራር ስርዓትን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የውዝፍ እዳ ክትትል ማጠናከር እና የጉምሩክ ዋጋን ወቅታዊ የማድረግ ስራ በቀጣይ ጊዜያት እንደሚከናወን አስታውቋል።

የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ልማት ስራዎችን ማጠናከር፣ አዳዲስ ታክስ ከፋዮች ወደ ታክስ ስርዓቱ እንዲገቡ ክትትል ማድረግ እንዲሁም የደረሰኝ እና የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ቁጥጥርና ክትትልን ማጠናከርና ሌሎች የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

ግብረ ኃይሉ በታክስ አስተዳደሩ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችሉ የታክስ ፖሊሲ፣ የሀገር ውስጥ ታክስ አስተዳደር እና በጉምሩክ ቀረጥና ታክስ አስተዳደር ጉዳዮች እቅድ በማዘጋጀት አፈፃፀሙን እየገመገመ እንደሚገኝም ከጉምሩክ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም