ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል- ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ።

አየር ኃይሉ ዋና አዛዡን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር የምግብ፣ አልባሳትና የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁሶች ድጋፍና ማዕድ ማጋራት መርኃ ግብር አካሂዷል።


 

ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ወቅት በማዕከሉ ጉብኝታቸው የተመለከቱትን ሰብዓዊነት ተግባር አድንቀው፤ ከራስ በፊት ህዝብና ሀገርን የሚያስቀድመው ሰራዊቱ መሰል ሰብዓዊ ተግባራትን ለመደገፍ ምንጊዜም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከፍተኛ አመራሮች በማዕከሉ ተገኝተው ላደረጉት ጉብኝትና ድጋፍም አመስግነዋል።

መቄዶንያ እያስገነባ ያለውን ግዙፍ ሁለገብ ህንፃ ለማጠናቀቅ የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ሀገራዊ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ማዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ በዚህ መርኃ ግብር ላይ ሁሉም ዜጋ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

መቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር በ44 ከተሞች ከ8 ሺህ በላይ ሰዎች ባሕላዊና መንፈሳዊ ፍላጎትና ክብራቸው ተጠብቆ እየተረዱ የሚገኝበት ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም