ቀጥታ፡

ጤና ሚኒስቴር ከ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያ ድጋፍ ተረከበ

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፡-አሲስት ኢንተርናሽናል 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዲሁም ሪች አናዘር ፋውንዴሽን  1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የሚገመት  የህክምና መሳሪያዎች ለጤና ሚኒስቴር አስረከቡ።

በርክክቡ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ እንዳሉት የጤና ሚኒስቴር ከበሽታ መከላከል ባለፈ አክሞ ማዳን ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ለውጥ በማድረግ አክሞ ማዳን ላይ ያለውን አቅም ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል።

ለዚህም የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የህክምና ግብዓትና የአተገባበር ስርዓቱን ለማሳለጥ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

አሲስት ኢንተርናሽናል የኦክሲጅን አቅርቦትና በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎች ስልጠና ላይ እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከአሲስት ኢንተርናሽናል የተገኘው የፅኑ ህሙማን ህክምና መገልገያ መሳሪያ ለተመረጡ ስምንት ሆስፒታሎች እንደሚከፋፈል ጠቅሰው እገዛው የአገልግሎት አሰጣጡን የሚያሻሽል ነው ብለዋል።


 

የአሲስት ኢንተርናሽናል ፕሬዝዳንት ራልፍ ሰድፊልድ በበኩላቸው ጤና ሚኒስቴር የአገሪቱን የጤና ስርዓት ለማጠናከር እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑንና ተቋማቸውም በዘርፉ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዛሬው እለትም ተቋማቸው ጂኢ ኸልዝ ኬር ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመሆን ያደረገው ድጋፍ በፅኑ ህክምና ላይ ላሉ ጨቅላና አዋቂ ህሙማን የሚረዳ እንደሆነም ጠቁመዋል። 

ሪች አናዘር ፋውንዴሽን በበኩሉ ለአራት ሆስፒታሎች 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር የሚገመት የኒዩሮሰርጂካል ማይክሮስኮፕ ድጋፍ አድርጓል።

ፋውነዴሽኑ በአገሪቱ በጥቂት ሆስፒታሎች ብቻ ያሉና የኒዩውሮ ወይም የጭንቅላት ቀዶ ህክምና ለመስጠት የሚያግዙ ማይክሮስኮፖች ድጋፍ አድርጓል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት የተደረገው የማይክሮስኮፕ ድጋፉ የጭንቅላትና ነርቭ ቀዶ ህክምናን ለመስጠት የሚያግዝ ዘመናዊ መሳሪያ መሆኑን ገልፀዋል። 


 

የሪች አናዘር ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ያዕቆብ ሰማን የዛሬውን ድጋፍ ጨምሮ 9 መሰል ማይክሮስኮፖች በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ለማሰራጨት መታቀዱን ተናግረዋል።

በአይደር ሆስፒታል የኒዩሮ ሰርጅን ትምህርት ክፍል ሀላፊ ዶክተር ሳምሶን ይባልህ ድርጅቱ ያደረገላቸው ድጋፍ የህክምና አገልግሎትና ትምህርት ክፍሉን ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።  

የማይክሮስኮፑ ድጋፍ የሚሰጡትን የህክምና አገልግሎት ጥራት ለማስጠበቅና በመጠን ለማሳደግ እንደሚረዳቸው የገለጹት ደግሞ የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም እሸቱ ናቸው። 

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም