ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖን ለመቀነስ የአየር ትንበያን ማዘመንና የመረጃ ተደራሽነትን ማስፋት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2017(ኢዜአ)፡- የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖን ለመቀነስ የአየር ትንበያን ማዘመንና የመረጃ ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ 69ኛ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

“የአየር ንብረት አገልግሎት፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ክፍተቶችን በጋራ ለመሙላት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ፎረም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን፣ የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል ከልማት አጋሮች ጋር አዘጋጅተውታል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በፎረሙ መክፈቻ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ የአለም ፈተና ቢሆንም በቀጣናው እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ተለዋዋጭ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ መንስዔ አስቀድሞ በማወቅ መረጃን ተደራሽ ማድረግ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የአየር ትንበያ አገልግሎትን ለማዘመን በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ዳይሬክተር አብዲ ፊዳ(ዶ/ር) በበኩላቸው አለምን እየፈተነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ የተቀናጀና የተናበበ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

ምስራቅ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ ተደጋጋሚ ተፅዕኖ የሚደርስበት እንደ መሆኑ ትንበያውን አስቀድሞ በማሳወቅ የቅድመ መከላከል ተግባር ማከናወን ይገባል ነው ያሉት።

በፎረሙ እ.አ.አ ከማርች እስከ ሜይ 2025 ያለው ቀጣናዊ የአየር ትንበያ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት በተተገበሩ ስትራቴጂዎች እና በተገኙ ውጤቶች ላይ ውይይት ይካሄዳል።

በፎረሙ የዘርፉ ተመራማሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችንና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም