በጎንደር እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ከተማዋን ወደ ከፍታ የሚወስዱ ናቸው

አዲስ አበባ፤ጥር 13/2017(ኢዜአ)፦በጎንደር እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ከተማዋን ወደ ከፍታ የሚወስዱ ናቸው ሲሉ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።

በጎንደር ከተማ ባለፉት አራት ዓመታት የፕሮጀክት አፈፃፀም ወደ 62 በመቶ ማደጉም ተገልጿል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ከከተማዋ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና አይ ኤች ኬሪዩትሊንን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው "የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" ኤግዚቪሽን እና ወይይት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው እንዳሉት፣ ጎንደር ለዓመታት የነበረችበትን የቁልቁለት ጉዞ ታሪክ ያደረገችበት የከፍታ ዘመን ላይ ትገኛለች።

የጎንደር ህዝብ ጥያቄ የነበረው የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥት በጥሩ ሁኔታ በመታደሱ ከመፍረስ ስጋት አልፎ የከተማዋ የውበት ምንጭ ሆኗል ብለዋል።

ጎንደርን የኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸው፤ እየተከናወኑ ያሉ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ከተማዋን ወደ ከፍታ የሚወስዱ ናቸው ብለዋል።

የጎንደር ከተማ የምትገኝበት የልማት ጎዳና የነበረችበትን የኋልዮሽ መንገድ የሚቀይር ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ጎንደርን የልማት ኮሪደር ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊደግፍና ወደ ሚመጥናት ማማ ማውጣት ይገባል ነው ያሉት።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ግርማይ ልጅዓለም በበኩላቸው ንግድና ኢንቨስትመንት በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ አይደለም ብለዋል።

በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት በጎንደር ከተማ የፕሮጀክት አፈፃፀም ከ53 በመቶ ወደ 62 በመቶ አድጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም