ቀጥታ፡

የአየር ንብረት ለውጥ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የኢጋድ አባል ሀገራት የአየር ጠባይ ትንበያ መሰረታቸውን ሊያሰፉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ጥር 12/2017(ኢዜአ)፦ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የኢጋድ አባል ሀገራት የአየር ጠባይ ትንበያ መሰረታቸውን ይበልጥ ሊያሰፉ እንደሚገባ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል ዳይሬክተር አብዲ ፊዳ (ዶ/ር) አስታወቁ።

69ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ትንበያ ፎረም (GHACOF) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።


 

በፎረሙ እ.አ.አ ከመጋቢት እስከ ግንቦት 2025 ያለው ቀጣናዊ የአየር ጠባይ ትንበያ ነገ ይፋ ይደረጋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ዳይሬክተር አብዲ ፊዳ (ዶ/ር) አለምን እየፈተነ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ የተቀናጀ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የተለያየ የአየር ጠባይ የሚስተናገድበት እንደመሆኑ የአየር ትንበያውን አስቀድሞ ማወቅና ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደሚገባ ነው ያነሱት።

ቀጣናው ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጎርፍ፣ድርቅ፣ የአንበጣ መንጋ እንዲሁም ወባና ኮሌራን የመሳሰሉ በሽታዎች ሲፈትኑት እንደነበርም አስታውሰዋል።

በአየር ንብረት ጠባይ መለዋወጥ ምክንያት ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ጫና አስቀድሞ ለመከላከል ሀገራት የትንበያ አቅማቸውን ይበልጥ ማሳደግና የመረጃ ተደራሽነትን ማስፋት እንዳለባቸውም አንስተዋል።

በተለይም የአየር ትንበያ መረጃዎች ለአርሶአደሩና ለአርብቶ አደሩ በትክክል ተደራሽ እንዲሆኑ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በፎረሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ የዓለም ፈተና ቢሆንም በቀጣናው እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋል።


 

ተለዋዋጭ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ አስቀድሞ ማወቅና መረጃን ተደራሽ ማድረግ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የአየር ትንበያ አገልግሎትን ለማዘመን በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የበጋ ወቅት የአየር ጠባይ ግምገማዋንና በቀጣይ በልግ ሊከሰት የሚችለውን የአየር ጠባይ ትንበያ በቀጣይ ሳምንት ይፋ እንደምታደርግም ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ማዕከሉ ነገ ይፋ የሚያደርገው መረጃ ሀገራት ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ትንበያቸውን ይፋ እንዲያደርጉ ያግዛል ብለዋል።


 

የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዋ ማስሊን ክሎሽባ አብዛኛው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ህዝብ በግብርና የሚተዳደር እንደመሆኑ የአየር ጠባይ ትንበያው ትልቅ እገዛ ያደርግለታል ብለዋል።

“የአየር ንብረት አገልግሎት፤የቅድመ ማስጠንቀቂያ ክፍተቶችን በጋራ ለመሙላት” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውን ፎረም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የአየር ንብረት ትንበያ እና የመተግበሪያ ማዕከል(ICPAC) ከልማት አጋሮች ጋር ያዘጋጁት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም