ቀጥታ፡

ብቁ የሰው ኃይል ከማፍራት እስከ የተቀናጀ የከተማ ግብርና ምርታማነት

የከተማ ግብርና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት በግለሰብ መኖሪያ አካባቢና የተለያዩ ተቋማት ውስጥ እየተተገበረ ይገኛል።

የትምህርት ተቋማትም በከተማ ግብርና ውጤታማ ስራ በመስራት ከሰራተኞቻቸው ፍጆታ አልፈው በተመጣጣኝ ዋጋ ለአካባቢው ማህበረሰብ እያቀረቡ ይገኛሉ።

የጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ካሉት የትምህርት ክፍሎች መካከል አንዱ የከተማ ግብርና ሲሆን በቅጥር ግቢው ውስጥ ለከተማ ግብርና ቦታ በመወሰን የተቀናጀ ግብርና በውጤታማነት እየሰራ ነው።

በዚህም የወተት ላም እርባታ፣የከብት ማድለብ ስራ፣ የጓሮ አትክልት፣ የአሳ እርባታና የዶሮ እርባታ ይገኙበታል።

በኮሌጁ የከተማ ግብርና ትምህርት ክፍል ኃላፊ አሰልጣኝ ታሪኩ በቀለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኮሌጁ ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች ባሻገር በተግባር በሌማት ትሩፋት ውጤታማ ስራዎችም እየሰራ ይገኛል።

ኮሌጁ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ዘመናዊ የወተት ልማት ማዕከል ገንብቶ ስራ መጀመሩን ጠቁመው ኮሌጁ ለሚሰጣቸው ስልጠናዎች የተግባር ልምምድ የሚካሄድበት ብሎም የወተት ምርት ለግቢው ማህበረሰብ በዝቅተኛ ዋጋ ተደራሽ እየተደረገበት ነው ብለዋል፡፡

ኮሌጁ እያከናወነ ያለው የከተማ ግብርና ስራዎችን ሰልጣኞች በተጨባጭ የልምምድ ተግባር የሚያከናወኑበት ከመሆን ባለፈ የተቋሙን ሰራተኛ መደጎም አላማ ያደረገ መሆኑንም ጠቁመው፥ ለአብነትም ወተት በሊትር እስከ 30 ብር በመሸጥ ላይ መሆናቸውን ይናገራል።

በዚህም ከወተት በወር 110 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፥ በዓመት ከ1 ሚሊዮን 320 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያስገኝም ጠቁመዋል፡፡

በተቋሙ በሚገኘው የጓሮ አትክልት እርሻም ተማሪዎች ተመርቀው የራሳቸውን ስራ እስኪጀምሩ ድረስ ስራውን እንዲከታተሉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ተቋሙ የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የእርድ ሰንጋዎች፣ የወተት እና አጠቃላይ የጓሮ አትክልቶች ለሽያጭ በማቅረብ ገቢ እያገኘበት እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻም፥ የከተማ ግብርና ስራዎቹ ከተግባር ስልጠና ባሻገር የሚገኘውን ምርት ለአካባቢው ማህበረሰብና ለተቋሙ ሰራተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

የኮሌጁ የአሳ እርባታ ማዕከልም የአሳ ጫጩቶችን መንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት በማከፋፈል ተጨማሪ ገቢ በማግኘት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የከተማ ግብርና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት በዚህ ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉም መክረዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም