ቀጥታ፡

የፋይዳ መታወቂያ የዲጂታል ማህበረሰብ መሰረተ ልማት ትግበራን ለማፋጠን ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2017(ኢዜአ)፦ የፋይዳ መታወቂያ የዲጂታል ማህበረሰብ መሰረተ ልማት ስራን ውጤታማ ለማድረግ ምቹ መደላድል መፍጠሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።

የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው የዲጂታል ፐብሊክ መሰረተ ልማት አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ ከብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፣ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመተግበር በርካታ ውጤቶች ማስመዝገቧን ገልጸዋል።

አዲስ የተቀረጸው የዲጂታል መንግስት ስትራቴጂ አካል በሆነው የዲጂታል ማህበረሰብ መሰረተ ልማት አማካኝነት በትግበራ ላይ የሚገኘው ፋይዳ መታወቂያ ዘርፉን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የቶኒ ብሌር ከፍተኛ አማካሪ እና የህንድ ኤሌክትሮኒክ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ኢንተርፕረነርሺፕ ሚኒስትር ራጂቭ ቻንድራሴክሃር ህንድ በዲጂታል መሰረተ ልማት ያስመዘገበችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ውጤት አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።

ስትራቴጂካዊ እቅዶችን በመተግበር የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን የማልማት ስራ ስኬት መመዝገቡን አመልክተዋል።

የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማለዳ ብስራት ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ለመንግስት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም