አቅም ያለው ለሌለው የማካፈል በጎ ተግባርን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል - ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል - ኢዜአ አማርኛ
አቅም ያለው ለሌለው የማካፈል በጎ ተግባርን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል - ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል
አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2017(ኢዜአ)፦ በዓላትን ስናከብር የተቸገሩትን በማሰብና ካለን በማካፈል በጎ ተግባርን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ገለጹ።
የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለያዩ መንፈሳዊ ስነ-ስርዓቶች በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል በድምቀት ተከብሯል።
የቤተ ክርስቲያኗ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ክብረ በዓሉ በማህሌት፣ ቅዳሴ፣ በመንፈሳዊ መዝሙሮች፣ በምስጋና ምዕመናኑን ፀበል በማጥመቅ መርሃ ግብር በአማረ መልኩ መከበሩን ተናግረዋል።
ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ ትህትናንና ፍቅርን ያስተማረበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የትህትና መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉን ከማክበር ባለፈም አቅመ ደካሞችን፣ የኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሰብና ያለንን በማካፈል በጎ ተግባር አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የታደሙ ምዕምናን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጠመቅ ያሳየው ትህትና እያንዳንዳችን ዝቅ ብለን እንድናገለግልና እንድንተባበር የሚያደርገን ነው ብለዋል፡፡
በዓሉን የሚያከብሩ ምዕምናን የትህትና መምህር የሆነውን የክርስቶስን የህይወት ፈለግ መመሪያ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
ይህም ለሰላም፣ ለአንድነት፣ እርስ በርስ በመተባበር እና አንዱ ለሌላው በማሰብ ሊሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ጥመቀት መዋደድ፣ መረዳዳት፣ ቂምን በመተው እርቅ በማስፈን መሆኑን በመረዳትና በተግባር በመግለጥ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ምዕመኑ በዓሉን ምክንያት በማድረግም የማዕድ ማጋራትና የአልባሳት ስጦታ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል የጥምቀት በዓል ሲከበር ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምዕመናንና የውጭ ሀገር ዜጎች ተገኝተዋል።