በክልሉ በመጀመሪያው ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ስኬታማ ናቸው - አቶ አብርሃም ማርሻሎ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በመጀመሪያው ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ስኬታማ ናቸው - አቶ አብርሃም ማርሻሎ

ሀዋሳ፤ ጥር 11/2017(ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል በመጀመሪያው የብልጽግና ፓርቲ ጉባዔ የተቀመጡ የልማት ግቦችንና አቅጣጫዎችን ለማሳካት በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን በፓርቲው የሲዳማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ አስታወቁ።
አቶ አብርሃም በክልሉ በፓርቲው በመጀመሪያው ጉባዔ የተቀመጡ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራዎችና የተገኙ ስኬቶችን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ አበረታች ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በፓርቲው የመጀመሪያ ጉባዔ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተደረጉ ጥረቶችና የተመዘገቡ ውጤቶች ለቀጣይ መነሳሳት የሚፈጥሩ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል።
በክልሉ ''ከቃል ወደ ባህል'' በሚል መሪ ሀሳብ የ2ኛው ጉባኤ የቅድመ ጉባኤ መድረኮች የልማት ስራዎችን ስኬትና የተስተዋሉ ጉድለቶችን በአግባቡ የተፈተሹበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም አበረታችና ለቀጣይ ስራ የበለጠ የሚያነሳሱ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በፖለቲካው ረገድም በክልሉ የዴሞክራሲ ግንባታን ማጠናከር በሚያስችል መልኩ የሐሳብ ልዩነቶችን እንደአቅም በመውሰድ አሳታፊ በሆነ መልኩ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዚህም አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበትና ልማት ላይ እንዲተኮር የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍም እንዲሁ እንደክልል ያሉትን አቅሞች በመለየት ሁሉንም ዜጋ በማሳተፍ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የቤተሰብ ብልጽግናን ማረጋገጥ በሚል ዕሳቤ የተለያዩ የልማት ግቦች ተቀርጸው ተግባራዊ የተደረጉ ሲሆን ውጤታማ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በዚህም እንደክልል በተሳትፎም ሆነ በስኬት ሁለንተናዊ ውጤት እንዲያመጣ የተቀመጡ ስምንት ኢንሼቲቮችና 67 ፓኬጆች እያስመዘገቡት ያለው ውጤት የሚያስደስት መሆኑን ገልጸዋል።
በሌማት ትሩፋትም በእንስሳት ሀብት በዝርያ ማሻሻልና በዶሮ እንዲሁም በዓሳ ሀብት ልማት የተመዘገቡ ተጨባጭ ውጤቶች የስራ ዕድል ፈጠራና ገበያን ማረጋጋት የቻሉ መሆናቸውንም አክለዋል።
የቡና ልማት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አምራቹን ተጠቃሚ ለማድረግ በተደረጉ ጥረቶች አኩሪ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ይህን ለማጠናከርም አቅጣጫ መቀመጡን አብራርተዋል።
በመንገድና ውሃ እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማት ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ የህዝብን ፍላጎት ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶች አበረታች ናቸው ብለዋል።
በማህበራዊ ዘርፍ በተለይም በትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን በክልሉ ከታችኛው ክፍሎች ጀምሮ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻልና የመምህራን አቅም ግንባታን በማካተት በተሰሩ ስራዎች በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻሎች መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በጤናው ዘርፍም እንዲሁ ተቋማትን በመገንባትና የህክምና ግብዓቶችን በማሟላት ህዝቡ የሚገባውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል የተደረጉ ጥረቶች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።
እነዚህ ስኬቶች እንዳሉ ሆነው በክልሉ ከዚህ በላይ ስኬት ማስመዝገብ እየተቻለ ጉድለቶች መኖራቸውን መገምገሙን ጠቅሰው እነዚህን በመፍታት ለቀጣይ የበለጠ ስኬት ለማስመዝገብ ይሰራል ብለዋል።
በፖለቲካው ዘርፍ ሁሉም ወጥ በሆነ መልኩ በጋራና በውይይት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ መሳሳቦች መኖራቸው እንዲሁም በተሰጣቸው የስራ ሃላፊነት በሚገባቸው መልኩ ያልመሩና ለህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ ያልሰጡ አካላት መኖራቸው መገምገሙንም አክለዋል ሃላፊው።
በእነዚህ አካላት ላይ ከታች ጀምሮ ጠንካራ የማጥራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለዩት ላይ ከቦታ ማንሳትን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በክልሉ 619 ሺህ 575 አባላት የተሳተፉበት ቅድመ ኮንፍረንስ ጉባዔ መካሄዱን ጠቅሰው፤ ክልሉን ወክለው በሀገር አቀፉ ጉባኤ የሚሳተፉ 86 አባላት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መመረጣቸውንም ተናግረዋል።