ጥምቀት ኢትዮጵያ የበርካታ ሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት መሆኗን አንዱ ማሳያ ነው - የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2017(ኢዜአ)፦ ጥምቀት ኢትዮጵያ የበርካታ የሀይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት መሆኗን አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ የታደሙ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ገለፁ።

ጎብኚዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር ስነ-ስርዓትን በመታደማቸው ልዩ ስሜት ፈጥሮባቸዋል።

ላለፉት 18 ወራት በኢትዮጵያ ቆይታ ማድረጋቸውን የሚገልጹት ከአሜሪካ የመጡት ኒያሚ ፌላስ የጥምቀት አከባበር አስገራሚ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያለው በዓል መሆኑን መመልከታቸውን ጠቅሰዋል።

ባለፈው አመት ከኢትዮጵያውያን ጋር የከተራ እለት ታቦታትን መሸኘታቸውን አስታውሰው ዛሬ ደግሞ በጃንሜዳ በመገኘት ሀይማኖታዊ ስርዓቱን መከታተላቸውን አንስተዋል።

በዓሉም ኢትዮጵያ አስገራሚና ውብ የሆኑ በርካታ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ሀብቶች እንዳሏት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ ሀገራት የጥምቀት በዓልን ቢታደሙም በኢትዮጵያ አከባበሩን መታደማቸው ልዩ ስሜትን እንደፈጠረባቸው የሚገልጹት ደግሞ ከኔዘርላንድ የመጡት ዶክተር ጆአኪም ፒርሰን ናቸው።


 

ከአሜሪካ የመጡት ኒያሚ በአዲስ አበባና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች የሚበረታቱና ጥሩ ውጤት ለሀገርና ለህዝቡ የሚያስገኙ መሆናቸውን እንደሚረዱም ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚጎበኙ በርካታ አስደናቂ ስፍራዎች መኖራቸውን መመልከታቸውን ጠቅሰው፤ ቱሪስቶች እነዚህን ስፍራዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት እንዲጎበኟቸው ነው የጠቆሙት።



 

ከብራዚል የመጡት አሪተን ሪቤሪዮ በበኩላቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜያቸው መሆኑን ገልፀው፤ በኢትዮጵያ ቆይታቸው በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የቱሪስት መስህቦችን መጎብኘታቸውንም ጠቅሰዋል።

ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጥምቀትንና ሌሎች በሀገሪቱ ያሉ መስህቦችን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።


 

ሌላው ከአሜሪካ የመጡት ዊልያም ሆትን በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ባህሎችና የመስህብ ስፍራዎች ሳቢ በመሆናቸው በመላው አለም የሚገኙ ጎብኚዎች እንዲጎበኟቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም