የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2017(ኢዜአ)፦ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች የጥምቀት በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የጥምቀት በዓል ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የደስታ እና የሀሴት እንዲሆን መልካም ምኞቱን ገልጿል።
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው ጥምቀት በዓሉ ላለው ቱባ ባህሎች፣ ልማዶች፣ ማህበረሰባዊ እውቀቶች እና አፋዊ አገላለጾች እውቅና የሰጠ መሆኑን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንላችሁ! ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
ለመላው የእምነቱ ተከታዮች በሙሉ መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንላችሁ! ሲል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን ያስተላለፈው ደግሞ በኢትዮጵያ የኢራን ኤምባሲ ነው።
በኢትዮጵያ የዚምባቡዌ እና ሞሮኮ ኤምባሲዎችም እንኳን ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ በዓሉ የደስታ እንዲሆን እንመኛለን ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ኦስትሪያ፣ ስዊድን፣ ካናዳ፣ ፓኪስታን ኤምባሲዎች በመልካም ምኞት መልዕክታቸው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለበዓሉ በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት አምባሳደር ቲቦር ናጅ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም የጥምቀት በዓል እንዲሆንላችሁ አምኛለሁ ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኤልኦ)) የአፍሪካ ቀንድ ቢሮዎች ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን ለእምነቱ ተከታዮች መልካም በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል።