ጥምቀት ኢትዮጵያውያን እሴታቸውን ጠብቀው ለትወልድ ማስተላለፍ እንደሚችሉ የሚያሳይ በዓል ነው - የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች - ኢዜአ አማርኛ
ጥምቀት ኢትዮጵያውያን እሴታቸውን ጠብቀው ለትወልድ ማስተላለፍ እንደሚችሉ የሚያሳይ በዓል ነው - የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች
አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2017(ኢዜአ)፡- ጥምቀት ኢትዮጵያውያን እሴታቸውን ጠብቀው ለትወልድ ማስተላለፍ እንደሚችሉ የሚያሳይ በዓል መሆኑን የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ገለጹ።
ጥምቀትን በጎንደር የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተሳተፉበት በድምቀት ተከብሯል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በበዓሉ አከባበርና በህዝቡ እንግዳ አቀባበል መደመማቸውን ገልጸዋል።
ስፔናዊው ጎንዛሎ ቦቴት የጥምቀት በዓል ኃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ የሚከበር ደማቅ በዓል መሆኑን ይገልጸዋል።
ገናን በላሊበላ እንደታደሙ ጠቅሰው፤ ጥምቀት ደግሞ ሌላኛው የኢትዮጵያ ድንቅ ሀብት ሆኖ ማየታቸውን ተናግረዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ካቀድኩ አምስት ዓመታት ባስቆጥርም ዘንድሮ ተሳክቶልኛል የሚሉት ታዳሚ ደግሞ ቡልጋሪያዊቷ ስቶያና ሩሲቮቫ ናቸው።
ጥምቀት እጅግ አስደናቂ ትዕይንተ የሚታይበት በዓል መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ጠብቃ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደምትችል የተገነዘቡበት መሆኑን ገልጸዋል።
ከፈረንሳይ የመጡት ፍራንሶይስ ላቫሎ ኢትዮጵያውያን እንግዳ በክብር የሚያስተናግዱ፣ በፍቅር የተሞላ ደግ ልብ ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብለዋል።
የጥምቀት በዓልም በየትኛውም የአውሮፓ ሀገር በዚህ ልክ በአለባበስ ደምቆና ሳቢ ሆኖ እንደማይከበር አንስተዋል።
ጥምቀትን በጎንደር ሳከብር የመጀመሪያዩ ነው፣ በጣም አስደናቂ ነው ያሉት ደግሞ ጣሊያናዊቷ ካሚላ ሪቸቲ ናቸው።
በዚህ ድንቅ ክብረ በዓል ላይ በመታደማቸው ደስታቸው ከፍ ያለ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ማንኛውም ተጓዥ ሊያያት የሚገባ ምቹ ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።
በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የነበረኝን ቆይታ በማህበራዊ ሚዲያ አጋርቸዋለሁ የሚሉት ቡልጋሪያዊቷ ስቶያና ሩሲቮቫ ህዝቡ ያለውን የሚያካፍል እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ኢትዮጵያ በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ ልትጎበኝ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ለጎብኚዎች ደግነትን የሚያወርሱ በመሆናቸው ከዚህ በኋላም በተደጋጋሚ መጎብኘት እንፈልጋለን ሲሉ የገለጹት ደግሞ፤ ስፔናዊው ጎንዛሎ ቦቴት እና ጣሊያናዊቷ ካሚላ ሪቸቲ ናቸው።