ህብረተሰቡ በመተሳሰብና በአብሮነት ለሀገር ሰላም እና እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ ይኖርበታል-ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፤ጥር 11/2017(ኢዜአ)፦ህብረተሰቡ እርስ በእርስ በመተሳሰብና በአብሮነት ለሀገር ሰላም እና እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ ይኖርበታል ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብረው ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ጥምቀት አንዱ ነው።

በአዲስ አበባ ጃንሜዳም የጥምቀት በዓል በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል።


 

ጥምቀት እየሱስ ክርስቶስ በባህረ ዮርዳኖስ በዮሃንስ መጠመቁን በማሰብ የሚከበር ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል እንደሆነ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመላው ሀገሪቱ የጥምቀትን በዓል እያከበሩ ለሚገኙ ምዕምናን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሰው ልጅ ዘላቂ ሕይወትን መቀዳጀት የሚችለው ፈርሃ እግዚአብሄርን መላበስ ሲችል ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ ፈጣሪ ከሰዎች የሚጠብቀውን መልካም ስብእናዎች ከመላበስና የአየር ንብረት ለውጥን ከመቆጣጠር አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮች የሰው ልጅን ለአደጋ ሲያጋልጡ ማስተዋል እየተለመደ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ሁሉም ቆም ብሎ ለመፍትሄው ማሳብ ይኖርበታል ብለዋል።

ሁሉም በፍቅርና በአብሮነት በመቆም ለሀገር ሰላም እና እድገት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት ነው የገለጹት።

ህብረተሰቡ ፈጣሪ የሰጠውን ጸጋ በመጠቀም እርስ በእርስ በመተሳሰብና በአብሮነት ለሀገር ሰላም እና እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ ይኖርበታልም ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው የጥምቀት በዓል በከተማዋ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ጥምቀት የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የዓለም ቅርስ ሆኑ የተመዘገበ የሀገር ሀብት መሆኑን አስታውሰው፣ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነቱ ባለፈ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን ከሀይማኖታዊ ሁነቱ ባለፈ የአለም ቅርስ በሆነው ከእምነቱ ተከታዮች ባለፈ የተለያዩ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ሲሳተፉ ማየት የተለመደ መሆኑን ተናግረዋል።

ጥምቀት ከበርካታ የአለም ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች የሚታደሙበት ደማቅ ሃይማኖታዊ በዓል በመሆኑ ሁላችንም የሀገራችን አምባሳደር በመሆን መልካም ገጽታን ለመገንባት የሚጠበቅብንን ሚና ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

የጥምቀት በዓል የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታያለው በመሆኑ መንግስት ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ተጠብቆ እንዲከበር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸው፥ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ምክትል ከንቲባው በመጨረሻም ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከበር ትህትናን በጎነት እና አብሮነት በሚያጠናክር መልኩ ሊያከብረው እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም