ቀጥታ፡

ጥምቀት ክርስቶስ ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ያስተማረበት በመሆኑ ምዕመኑ ይህንኑ ሊተገብር ይገባል - ብጹዕ አቡነ በርናባስ

ሰቆጣና/መተማ፤ ጥር 11/2017(ኢዜአ)፡- ጥምቀት ክርስቶስ ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ያስተማረበት በመሆኑ ምዕመኑ ይህንኑ ሊተገብር ይገባል ሲሉ የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ በርናባስ አስገነዘቡ።

ምዕመናን የጥምቀት በዓልን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመርዳትና አንድነትንና ፍቅርን በማስቀደም ሊያከብሩት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓል በዋግ-ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማና በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

ብጹዕነታቸው በስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ የጥምቀት በዓል የነፃነት፣ የፍቅርና የደስታ በዓል ነው።


 

ጥምቀት ክርስቶስ ሰላምን፣ ፍቅርንና አንድነትን ያስተማረበት በመሆኑ ምዕመኑ አንድነትንና ፍቅርን በማስቀደም ማክበር እንደሚገባው ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓልን ምዕመኑ አንድነቱንና ሰላሙን በማስጠበቅ ማክበር እንዳለበትም መክረዋል።

እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመርዳት ማክበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።


 

የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጌትነት እሸቱ በበኩላቸው፤ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባለፈ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክር እሴት ነው ብለዋል።

በጥምቀት በዓል የቀደሙ ቅሬታዎችን በይቅርታ በመሻር ፍቅርን የምናሰፍንበት ትልቅ በዓል ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ምዕመኑ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ረገድ እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።


 

በተመሳሳይም ጥላቻን በማስወገድ በአንድነትና በፍቅር በዓሉን ማክበር ይገባል ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ አዕላፍ ቆሞስ አባ ሀይለማርያም ያሳይ ናቸው።

በዚህም እርስ በእርስ መደማመጥ፤ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመነጋገር መፍታት እና ለሰላም በጋራ መስራት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

ቂም ይዞ መፀለይ የለምና ጥልን በማስወገድ ይቅር መባባልን ማስቀደም ይኖርብናል ሲሉም ገልፀዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኃላፊ አቶ አለሙ ጌታቸው እንዳሉት፤ በጥምቀት በዓል የሚታየውን መከባበርና አብሮነት ማስቀጠል ይገባል።

የዚህ ዓመት የጥምቀት በዓል ከቀደሙት ጊዜያት በተሻለ ሁኔታ ደማቅና በርካታ ህዝብ የታደመበት መሆኑንም ገልፀዋል።

የጥምቀት በዓልን ለማክበር የተፈጠረውን ህብረትና አንድነትም በቀጣይ በሌሎች የሰላም ማስከበርና የልማት ስራዎች ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

በገንዳ ውሃ ከተማ የጥምቀት በዓል አከባበር የወጣቶች አስተባባሪ ወጣት ሰለሞን እማኘው በበኩሉ፤ የጥምቀት በዓል አከባበሩ የተሳካ እንዲሆን በርካታ ወጣቶች ተሰማርተው እየሰሩ ነው ብሏል።

በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ሲሆን በቀጣይም አብሮነትና መከባበርን ለማስቀጠል እንደሚሰሩም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም