ሁላችንም በፍቅርና በአንድነት በመቆም ለሀገር ሰላምና እድገት የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል-ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ - ኢዜአ አማርኛ
ሁላችንም በፍቅርና በአንድነት በመቆም ለሀገር ሰላምና እድገት የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባል-ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
አዲስ አበባ፤ጥር 11/2017(ኢዜአ)፦ሁላችንም በፍቅርና በአንድነት በመቆም ለሀገር ሰላም እና እድገት የሚጠበቅብንን ሃላፊነት ልንወጣ ይገባል ሲሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው ሃይማኖቶታዊ በዓላት መካከል ጥምቀት አንዱ ነው።
በአዲስ አበባም በጃንሜዳ የጥምቀት በአል በልዩ ልዩ ሀይማኖታዊ ክንዋኔዎች በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል።
ጥምቀት እየሱስ ክርስቶስ በባህረ ዮርዳኖስ በዮሃንስ እጅ መጠመቁን በማሰብ የሚከበር ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል እንደሆነ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በመላው ሀገሪቱ የጥምቀትን በዓል እያከበሩ ለሚገኙ ምዕምናን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሰው ልጅ ዘላቂ ሕይወትን መቀዳጀት የሚችለው ፈርሃ እግዚአብሄርን መላበስ ሲችል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ ፈጣሪ ከሰዎች የሚጠብቀውን መልካም ስብእናዎች ከመላበስ አኳያ የሚስተዋሉ ችግሮች የሰው ልጅን ለአደጋ ሲያጋልጡ ማስተዋል እየተለመደ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ሁሉም ቆም ብሎ ስለሰላም ማሰብ ይኖርበታል ብለዋል።
ሁሉም በፍቅርና በአብሮነት በመቆም ለሀገር ሰላም እና እድገት የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበት ነው የገለጹት።
ህብረተሰቡ ፈጣሪ የሰጠውን ጸጋ በመጠቀም እርስ በእርስ በመተሳሰብና በአብሮነት ለሀገር ሰላም እና እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ ይኖርበታልም ብለዋል።