ጥምቀት በርካታ ጎብኚዎች የሚታደሙበት ደማቅ በዓል በመሆኑ የሀገራችንን መልካም ገጽታ ለመገንባት ሚናችንን ልንወጣ ይገባል - አቶ ጃንጥራር አባይ - ኢዜአ አማርኛ
ጥምቀት በርካታ ጎብኚዎች የሚታደሙበት ደማቅ በዓል በመሆኑ የሀገራችንን መልካም ገጽታ ለመገንባት ሚናችንን ልንወጣ ይገባል - አቶ ጃንጥራር አባይ
አዲስ አበባ፤ጥር 11/2017(ኢዜአ)፡-ጥምቀት ከበርካታ የአለም ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች የሚታደሙበት ደማቅ ሃይማኖታዊ በዓል በመሆኑ ሁላችንም የሀገራችንን መልካም ገጽታ ለመገንባት የሚጠበቅብንን ሚና ልንወጣ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ከምታከብራቸው ዓበይት በዓላት መካከል ጥምቀት ተጠቃሽነው።
በዓሉም ከከተራ እለት ጀምሮ በአደባባይ በርካታ የኃይማኖቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀት የሚከበር መሆኑይታወቃል።
በዚህም በመላው ሀገሪቱ ከትናንት ጀምሮ በተለያዩ ኃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች በመከበር ላይ ይገኛል።
የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው ጃንሜዳ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ የኃይማኖት አባቶች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች እና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አዲስ አበባ ከተማ በህብረ ብሄራዊነት የተዋበች ከተማ በመሆኗ የተለያዩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት በድምቀት የሚከበሩባት መሆኗን ጠቅሰዋል።
የጥምቀት በዓልም በከተማዋ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓቱን ጠብቆ እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ጥምቀት የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ የሀገር ሀብት መሆኑን አስታውሰው፣ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነቱ ባለፈ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥምቀት ከበርካታ የአለም ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች የሚታደሙበት ደማቅ ሃይማኖታዊ በዓል በመሆኑ ሀላችንም የሀገራችን አምባሳደር በመሆኑ መልካም ገጽታን ለመገንባት የሚጠበቅብንን ሚና ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከበር ትህትናን በጎነት እና አብሮነት በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።
የጥምቀት በዓል የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታያለው በመሆኑ መንግስት ሃይማኖታዊ ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲከበር የሚጠበቅበትን እያበረከተ መሆኑንም አንስተዋል።