ጥምቀት የሰላም ነጋሪት የተጎሰመበት በዓል በመሆኑ ሰላምን በተግባር መኖር ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ጥምቀት የሰላም ነጋሪት የተጎሰመበት በዓል በመሆኑ ሰላምን በተግባር መኖር ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2017(ኢዜአ)፡- ጥምቀት የሰላም ነጋሪት የተጎሰመበት በዓል በመሆኑ እርስ በእርስ በመከባበር ሰላምን በተግባር መኖር እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ጥምቀት በጎንደር ፋሲለደስ ባህረ ጥምቀት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች እና በርካታ ምዕመናን በታደሙበት በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በክብረ በዓሉ ላይ እንደገለጹት፤ ከለውጡ መንግሥት ወዲህ የጎንደር ከተማን የሚመጥኑ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ነው።
በመንገድና በውሃ ፕሮጀክት መሰረተ ልማት እንዲሁም በፋሲል ግንብ እድሳት የታየው ለውጥ የዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
ጥምቀት የሰላም የፍቅር የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን በመረዳት ሁሉም አካላት ለሰላም ዘብ መቆም እንዳላባቸው ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው ጎንደር ከተማ የጥር ሙሽራ መሆኗን ገልጸዋል።
ጎንደር ደምቃና አብባ ጥምቀት መገለጫዋ መሆኑን እያሳየች ነው ሲሉም አንስተዋል።
ከለውጡ በፊት በነበሩ ዓመታት ጎንደር ከሚመጥናት የእድገት ማማ ወርዳ በጨለማ ውስጥ መቆየቷንም ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ በለውጡ መንግስት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ መሰረት ለጎንደር ትንሳኤ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።