ጥምቀት በወጣት ምዕመናን አንደበት

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2017(ኢዜአ)፦ የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ አንድምታው ባሻገር ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶቹ የሚናፈቅ መልኮች እንዳሉት በአዲስ አበባ የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ታዳሚ ምዕመናን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በአደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት ዋዜማ የሆነው የከተራ ስነ ስርዓት በመላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተከውኗል።

በተለያዩ የባህል አልባሳት ደምቀው በአዲስ አበባ ጃንሜዳ ጥምቀተ ባሕር የተገኙ የበዓሉ ተሳታፊዎች፣ ጥምቀት ከሃይማኖታዊ አንድምታው ባሻገር ማህበራዊና ባህላዊ መልኮች ለሀገር ገጽታ ግንባታ ይበጃል ይላሉ።

በዚህም ለውጭ እንግዶች ቀርቶ ለሀገሬው ሰውም ሁሌም የሚናፍቅ የብዙሃኑን ቀልብ የሚስብ ትዕይንት እንደሆነ ይናገራሉ።

ኢዜአ ካነጋገራቸው ወጣቶች መካከል ብሌን ጌቱ፣ ህይወት ንብርጋ እና ሃይማኖት ኃይሉ እንደሚሉት የከተራና የጥምቀት በዓል ልዩ ሃይማኖታዊ አንድምታ ያለው ነው።

በሌላ በኩል ሁሉም በአቅሙ በባህል አልባሳት ደምቆ የሚወጣበት በመሆኑ የበርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ ይስባል ይላሉ።

ጥምቀት የኢትዮጵያ ባህል ለዓለም እንዲተዋወቅ ትልቅ አስተዋጾኦ ያለው በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሀገሩን ለማስተዋወቅ ጥረት ማድረግ እንዳለበት በመጠቆም።

የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ዝቅ በማድረግ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባህር መጠመቁ ትህትናን ለማስተማር እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመሆኑም በዓሉን ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አብሮነትንና መተሳሰብን በሚጠናክር መልኩ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገቡ ኢትዮጵያን በዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቅሰው፥ ሁሉም ዜጋ ለሀገር ገፅታ ግንባታ መስራት እንዳለበት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም