ቀጥታ፡

በጎንደር የከተራ ትዕይንቶች የተደነቁት አውሮፓዊያን ቱሪስቶች

የምድረ ቀደምቷ ሀገር ኢትዮጵያ ዕልፍ ዘመናት ሳይበረዙና ሳይደበዝዙ የተሻገሩ መልከ ብዙ ባህላዊና ኀይማኖታዊ ከዋኔዎች አሏት።

በየዘመናቱ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ያሉ የተለያዩ ክፍላተ ዓለማት እንግዶች በእነዚህ ባህላዊ ኃይማኖራዊ ክዋኔዎች የነበራቸውን ተመስጦ ከትበዋል።

ብዙ ምዕተ ዓመታትን ካስቆጠሩ ኃይማኖታዊ የአደባባይ ክዋኔዎች መካከል ደግሞ በማይዳሰስ ወካይ ዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት ክብረ በዓል ይጠቀሳል።

ከሶስት ምዕተ ዓመታት በፊት የነገስታት መናገሻ በነበራቸውና በርካታ የውጭ ሀገራት አሳሾችን ቀልብ የሳበችው ጎንደር፤ ዛሬም የእንግዶቿ መዳረሻ ናት።

የጥምቀትን ክብረ በዓል በልዩ ትዕይንትና ድምቀት በየዓመቱ የምታስተናገደው ጎንደር ከተማም ዘንድሮ ታሪካዊ ቅርሶቿን አድሳ፣ ዳግም ተሞሽራ የሀገር ውስጥም፣ የውጭም እንግዶቿን ተቀብላለች።

እንግደቿም በአብያተ መንግሥታቱና በሌሎች ታሪካዊ ቅርሶች በተጨማሪ በጥምቀት ልዩ የአደባባይ ክዋኔዎች ከወዲሁ እየተደነቁ ነው።

በዛሬው የጥምቀት ከተራ በዓልም ጎንደር ላይ የተገኙት የአውሮፓዊቷ ሀገር የቼክ ሪፐብሊክ ዜጋ ሮበርት ፍረንከል፤ ኢትዮጵያ የበርካታ አስደናቂ ትውፊቶች ባለቤት ናት ይላሉ።

ለዚህም በኢትዮጵያ የተለያዩ ክብረ በዓላት እየተመላለሱ እንደሚሳተፉ ይናገራሉ።

ዘንድሮም የተለመደ የኢትዮጵያዊያን እንግዳ አቀባበል ተስተናግደው ጎንደር ላይ ከተራን እንደታደሙ ገልጸዋል።

በዓለም ላይ የተለያዩ የአደባባይ ትዕይንቶች ቢኖሩም የጥምቀት ጨምሮ ሌሎች ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትዕይንቶች በጣም እንደሚያስደንቃቸው ይናገራሉ።

ዴንማርካዊው ክኑድ ሄደንስቴ በበኩላቸው ከሰሜን እስከ ደቡብ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውሬ ጎብኝቻለሁ ይላሉ።

በየካባቢው አስደናቂ ባህል፣ ድንቅ ተፈጥሮና እንግዳ ተቀባይ ህዝብ እንዳገኙ ገልጸው፤ በጉብኝታቸው ሁሌም ደስተኛ ናቸው።

ጥምቀት አያሌ ህዝብ በአንድነትና በደስታ ተሰባስቦ የሚያከብረው ሁነት በመሆኑ ሁሉም የውጭ እንግዳ ቢታደም የሚወደም ሁነት ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ህዝብ በማንኛውም ጊዜ ተባባሪና ቀናዒ፣ እና እንግዳ ተቀባይ በመሆኑም የህዝቡን ባህልና ቋንቋ ለማወቅ ጉጉት እንዳደረባቸው ገልጸዋል።

በዚህም አሁን የአማርኛ ቋንቋ መልመድ እንደጀመሩ ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ የውብ ተፈጥሮና ሰው አክባሪ ህዝብ መገኛ መሆኗን የገለጹት ጎብኝዎቹ፣ የኢትዮጵያን አስደናቂ የቱሪዝም መስህቦች ሁሉም እንዲጎበኘው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም