ቀጥታ፡

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለጥምቀት በዓል እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2017(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሰት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የጥምቀት በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክታቸው ጥምቀት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ በዓል መሆኑን በመግለጽ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸው መንግስት የግጭት ምዕራፍን ለመዝጋት የፍቅርን ድልድይ ለትውልዱ ለመገንባት በቁርጠኝነትና በታማኝኘት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዚህም በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የነበሩ አለመግባባቶችን በመፍታት ስላምና እርቅን በማወጅ ከሁሉም ለሁሉም የሆነ የሀገር ግንባታን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ወደ ውድቀት የሚመሩ መንገዶችን በመተው ወደ አንድነትና ወንድማማችነት የሚወስዱ እሴቶችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የሰላም በርን በመክፈትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፋን ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረም የሰላም አየር እንዲነፍስ አስችሏል፡፡

የመንግስትና የህዝብን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ መንገድ መምጣት ህዝብን ማክበር መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ የክልሉ መንግስት በአንድ እጁ ሰላምን ለማረጋገጥ በሌላኛው ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት አዲስ የቀበሌ አስተዳዳርን ተግባራዊ በማድረግም ህዝቡ የአገልግሎት አሰጣጥን በአካባቢው እንዲያገኝ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

ከድህነት አዙሪት ለመውጣት ዘርፈ ብዙ ስራዎች መጀመራቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ህዝቡ በክረምት ወራት በዝናብ እና በበጋውም ወራት መስኖን በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነት ለመላቀቅ መሠረት የሚሆኑ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ከክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመው ሁሉንም ወቅቶች ለልማት ማዋል ይገባልም ብለዋል፡፡

ለዚህ ስኬታማነትም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ለህዝቡ የገባነውን ቃል በተግባር እውን ማድረግ እንደጀመርነው ሁሉ አሁንም አጠናክርን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

በዓሉ የፍቅር፣ የእርቅ፣ የአንድነት፣ የተቸገሩትን የሚረዱበት በዓል እንዲሆንም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም