የጥምቀት በዓል የሕዝቦች አንድነት፣ ፍቅር፣ ትህትና እና አብሮነት የሚንፀባረቅበት ነው- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓል የሕዝቦች አንድነት፣ ፍቅር፣ ትህትና እና አብሮነት የሚንፀባረቅበት ነው- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2017(ኢዜአ)፡-የጥምቀት በዓል የሕዝቦች አንድነት፣ ፍቅር፣ ትህትና እና አብሮነት የሚንፀባረቅበት ልዩ በዓል መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጡሩ ራሱን ዝቅ አድርጎ የተጠመቀበት የትህትና በዓል ነው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የሚከበር አስደናቂ ትዕይንት የሚታይበት ተወዳጅ በዓል መሆኑንም አመልክተዋል።
የጥምቀት በዓል የሕዝቦች አንድነት፣ ፍቅር፣ ትህትና እና አብሮነት የሚንፀባረቅበት ልዩ በዓል እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀቱ ያሳየውን ትህትና ሁላችንም ዝቅ ብለን እንድናገለግልና እንድንተባበር የሚያደርገን በመሆኑ ይህን አስተምሮ በመተግበር ለአንድነትና ለሰላም መትጋት ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።
የበዓሉ አከባበር ከሃይማኖታዊ እሴቱም ባለፈ አብሮነትና መተባበር የሚታይበት የፍቅርና የአንድነት ማሳያ በመሆኑ ሁላችንም በአንድነት ለአከባቢያችን ሰላም ዘብ ከመቆም ባሻገር ለሁለንተናዊ ዕድገት የድርሻችንን ለመወጣት ቃል መግባት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዓሉ መላው የኢትዮጵያ ብሎም የክልሉ ነዋሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ቱሪስቶችና ለዓለም ማህበረሰብ ፍቅርን፣ ትብብርን፣ትህትናንና አንድነትን የሚያሳዩበት በዓል መሆኑንም እንዲሁ።
የክልሉ ነዋሪ በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን በተለመደው ጨዋነት በተሞላዉ የኢትዮጵያዊነት ባህል ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።