በጎንደር ከተማ ለጥምቀት በዓል የቀረቡ የባህል አልባሳት በጥራት፣ በዲዛይንና በዋጋ የተሻሉ ናቸው-- ሸማቾችና ነጋዴዎች  


 

ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 10/2017 ዓ.ም--በጎንደር ከተማ ለጥምቀት በዓል የቀረቡ የባህል አልባሳት በጥራት፣ በዲዛይንና በዋጋ የተሻሉ መሆናቸውን ሸማቾችና ነጋዴዎች ተናገሩ። 

የባህል አልባሳቱ ለጥምቀት በዓል መድመቂያ በመሆናቸው ከዘመኑ ጋር በሚሄዱ ዲዛይኖች ተዘጋጅተው በስፋት መቅረባቸውንም ገልጸዋል።  

"ኢትዮጵያውያን ከምንታወቅባቸው አንዱ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የባህል አልባሳቶቻቸን ነው" ያሉት በከተማው ቅዳሜ ገበያ የባህል አልባሳት ሲገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሰናይት መላኩ ናቸው።

የጥምቀት በዓልን በሃገር ባህል አልባሳት ተውቦ ለመዋል የባህል ቀሚስ በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

ወይዘሪት መሰረት መኳንት በበኩሏ፤ "ጥምቀት በባህል አልባሳት ተውበንና አምረን የምናከብረው ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓላችን ነው" ስትል ተናግራለች።

ወጣቱን ትውልድ ባማከሉ አዳዲስ ዲዛይኖች የተዘጋጁ የባህል አልባሳት ለዘንድሮ የጥምቀት የበዓል ገበያ ላይ በየአይነቱ እንደቀረቡ ማየቷን ጠቁማ፤ "በተሻለ ጥራት የተዘጋጁ አልባሳት በበቂ መጠን በተሻለ ዋጋ ስለቀረቡ እየሸመትን ነው" ብላለች።


 

የገቢ አቅምንና የዕድሜ ደረጃን አማክለው የተዘጋጁ ባህላዊ አልባሳት በዘንድሮ የጥምቀት በዓል በስፋት ለሽያጭ እንደቀረቡ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ሀረገወይን ልሳነወርቅ ናቸው።

የባህል አልባሳትን በመሸጥ ሥራ ለብዙ ዓመታት መቆየታቸውን ገልጸው፣ ለጥምቀት የባህል አልባሳት ገበያ መድመቁንና ገዢዎችም እንደ ምርጫቸውና ፍላጎታቸው እየሸመቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ባለፈው ዓመት ለጥምቀት በዓል የባህል አልባሳት ገበያ የተቀዛቀዘ እንደነበርና ዘንድሮ የተሻለ የገበያ እንዳለ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ፍሬህይወት ታምሩ ናቸው። 

እንደእሳቸው ገለጻ የባህል አልባሳቱ በጥራትም ሆነ በዲዛይን ተሻሽለው የተዘጋጁ ናቸው። 

የጎንደር የባህል ቀሚስ እንደ ጥራት ደረጃው ከ4 ሺህ ብር እስከ 5 ሺህ ብር በመሸጥ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በተለያዩ ዲዛይኖች ሰፍቶ ያዘጋጃቸውን የባህል አልባሳት ለጥምቀት በዓል በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ሀምዛ ሰኢድ ነው።


 

የዘንድሮው የከተራና የጥምቀት በዓል የዋዜማ ድባብ ደማቅና አስደሳች መሆኑንም ሸማቾችና የባህል አልባሳት ነጋዴዎቹ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም