የፕሪሚየር ሊጉ የ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የፕሪሚየር ሊጉ የ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥር 10/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋል።
ድሬዳዋ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
በጨዋታዎቹ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ19 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል።
በአምስቱ ጨዋታዎች ስምንት ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ስድስት ግቦችን አስተናግዷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ21 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
የ15ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ስሑል ሽሬ እና አርባምንጭ ከተማን ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ያገናኛል።
ስሑል ሽሬ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሶስቱ ሲሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ11 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
አርባምንጭ ከተማ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል።
በአምስቱ ጨዋታዎች አራት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ ስድስት ጎሎችን አስተናግዶ በ16 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የሊጉ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ይካሄዳል። ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመቀሌ 70 እንደርታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና የ15ኛ ሳምንት አራፊ ቡድኖች ናቸው።
የ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
መቻል በ25 ነጥብ ሊጉን እየመራ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን እና ሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 23 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የድሬዳዋ ከተማው መሐመድ ኑር ናስር፣ የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ እና የመቻሉ ሽመልስ በቀለ በተመሳሳይ ስድስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በጋራ እየመሩ ነው።
የአዳማ ከተማዎቹ ነቢል ኑሪ እና ስንታየሁ መንግስቱ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ፍጹም ጥላሁንና አማኑኤል ኤርቦ፣ የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ፣ የወላይታ ድቻው ያሬድ ዳርዛ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ እና ዩጋንዳዊው ቻርልስ ሙሲጌ በተመሳሳይ አምስት ግቦች ይከተላሉ።