ቀጥታ፡

አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

አዲስ አበባ፤ ጥር 9/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል።

አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ከዚህ ቀደም የሃዋሳ ከተማ ሴቶች ቡድን እንዲሁም ያለፉትን ሶስት ዓመታት የአርባምንጭ ከተማ ሴቶች ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ሲሰሩ መቆያታቸውን ገልጿል።

ባለፈው ዓመት በጋና አክራ የአፍሪካ ጨዋታዎች ላይም የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ማሰልጠናቸውን አስታውሷል። 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብሰባ አሰልጣኝ ዮሴፍ የብሔራዊ ቡድኑን ኃላፊነት እንዲረከቡ ውሳኔ አሳልፏል።

አሰልጣኙም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ለማሰልጠን እንዲሁም የአርባምንጭ ከተማ ኃላፊነታቸውን በመልቀቅ ሙሉ ለሙሉ ትኩረታቸውን ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ለማድረግ ተስማምተዋል። 

አሰልጣኝ ዮሴፍ ከአንድ ወር በኋላ በ2026 የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመርያ ዙር ዩጋንዳን የሚገጥመውን ቡድን በማዘጋጀት የብሔራዊ ቡድን ሥራቸውን እንደሚጀምሩ  የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም