የጥምቀት በዓልን በጎንደር ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን እየተቀበልን ነው-አቶ ቻላቸው ዳኘው - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓልን በጎንደር ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን እየተቀበልን ነው-አቶ ቻላቸው ዳኘው
አዲስ አበባ፤ጥር 9/2017(ኢዜአ)፦የጥምቀት በዓልን በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን እየተቀበሉ መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፥ የከተራና የጥምቀት በዓልን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ጎንደር በጥር ይበልጥ የምትደምቅ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ እሴቶች ያሉባት ከተማ ነች ብለዋል።
እንግዳ አክባሪው የጎንደር ህዝብ እና ሆቴሎች የበዓሉ ታዳሚዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ሰባት በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የቱሪዝም ሀብቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ እነሱን ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎንደር አብያተ መንግሥታት የመንግስት አስተዳደርን ጭምር የያዙ የሀገር ቅርሶች በመሆናቸው የመላ ኢትዮጵያውያን ሀብት ናቸው ብለዋል።
ጥምቀት ከሀይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎች በተጨማሪ የኢኮኖሚ መሰረታችን ጭምር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ በረራዎችን በመፍቀድ አስፈላጊ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት በርካታ እንግዶች እንዲገቡ በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል።
ከተራና ጥምቀትን በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን እየተቀበሉ መሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገልጸዋል።
የፋሲል ግንብ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ በተደረገለት ዕድሳት ወደ ድንጋይ ፍርስራሽነት ለመቀየር ከደረሰበት ደረጃ መታደግ ተችሏል ብለዋል።
እድሳቱ እና የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ገጽታ የሚቀይር፣የቱሪዝም ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ፣ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል።